የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ለ3ኛ ጊዜ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ ለ3ኛ ጊዜ መራዘሙ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ፥ የፕሬዚዳንት እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫው በፊፋ ጥያቄ መሰረት መራዘሙን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ የካቲት 24 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን ነው ፌዴሬሽኑ የገለፀው።

ፊፋ ለፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ ምርጫውን ለማካሄድ በቅድሚያ መጣራት ያለባቸው ጉዳዮች በመኖራቸው፤ የፊፋ እና የካፍ ተወካዮች በአፍሪካ ዋንጫ ቻን ውድድር ምክንያት ምርጫው ላይ መገኘት እንደማይችሉ እና ከምርጫው በኋላ ሊፈጠር የሚችል ችግሮችን ለማስቀረት እንዲቻል ምርጫው ከጥር 27 በኋላ እንዲካሄድ ጠይቋል።

በፊፋ ጥያቄ መሰረትም የምርጫ ስብሰባው የካቲት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንዲካሄድ መወሰኑን ነው ፌዴሬሽኑ በላከው መግለጫ ያስታወቀው።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ምርጫ መጀመሪያ ሊካሄድ ተይዞለት የነበረው ቀን ህዳር 1 2010 ዓ.ም እንደነበረ ይታወሳል።

ሆኖም ግን በወቅቱ በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፌዴሬሽኑ አባላት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ምርጫው በ45 ቀናት እንዲራዘም ተወስኖ ምርጫውን ታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ለማድረግ ቀን ተቆርጦ ነበር።

ሆኖም ታህሳስ 16 ቀን 2010 ዓ.ም ሊደረግ የነበረውን ምርጫም ፌዴሬሽኑ በድጋሚ ለጥር 5 2010 ዓ.ም አዘዋውሮት የነበረ ሲሆን፥ የምርጫው ቀን አሁን ሲራዘም ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።