በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄዱ 6 የማራቶን ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የግማሽ ማራቶን እና የማራቶን ሩጫ ውድድሮች ተካሂደዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ስድስቱ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሳተፉ ሲሆን፥ በአብዛኛውን ውድድሮችንም በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ችለዋል።

በዚህም መሰረት በትናትናው እለት በቻይና ዢያመን ከተማ በተካሄደው ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል።

ውድድሩን ደረጀ ደበላ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ በመግባት በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ ታሪኩ በቀለ በ2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ 2ኛ፣ አየለ አብሽሮ 2 ሰዓት ከ11 ደቂቃ ከ33 ሰከንድ 3ኛ እንዲሁም ደርቤ ሮቢ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ በመግባት 4ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

ሲሳይ ሀይለሌ እና ጤናው በለጠ የተባሉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም 6ኛ እና 8ኛ ደረጃን በመያዝ ውደድሩን አጠናቀዋል።

በሴቶች በተደረገ ውድድር ደግሞ ፋጡማ ሳዶ 2 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ41 ሰከንድ 1ኛ፣ ሂሩት አለማየሁ 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ 2ኛ፣ መሰረት መንግስቱ 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ 3ኛ ሲወጡ፤ ትእግስት ማሙዬ እና ለምለም በርሄ ደግሞ 4ኛ እና 5ኛ በመውጣት ውደድሩን አጠናቀዋል።

በተመሳሳይ በእስራኤል ታይቤሪያስ በትናንትናው እለት በተደረገው የማራቶን ውድድርም በሴቶች ኢትዮጵያዊት አትሌት አሸንፋለች።

አትሌት አያንቱ አበራ ደምሴ 2 ሰዓት ከ40 ደቂቃ ከ37 ሰከንድ በመግባት ውድድሩን በአንደኝነት ማጠናቀቅ ችላለች።

በግማሽ ማራቶን ውድድር፤ ትናንት በቱርክ ኢስታንቡል በተካሄደው ኤድና ግማሽ ማራቶን በወንዶች ፈጠነ አለሙ እና ጌታዬ ገላው 6ኛ እና 8ኛ ሆነው ውድድሩን ሲያጠናቅቁ፤ በሴቶች ብዜነሽ ጌታቸው እና ኮንጂት ጥላሁን 4ኛ እና 5ኛ በመውጣት ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በሞሮኮ በተካሄደው ሳፊ ግማሽ ማራቶን በወንድም በሴትም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል።

በወንዶች በተካሄደው ውድድር ጌታነህ ታምሬ በ1 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ01 ሰከንድ 1ኛ በመውጣት ውድድሩን ሲያሸንፍ፤ ግዛቸው ሀይሉ 4ኛ፣ አዳነ ውለታው 7ኛ፣ አበባው ባየህ 9ኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን አጠናቀዋል።

በሴቶች መሰረት በለጠ ቶላ 1 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ 1ኛ ሆና ውድድሩን ስታጠናቅቅ፤ ዘነቡ ፍቃዱ፣ ሄቨን ሀይሉ እና ዝናሽ ደበበ ከ5 እስከ 7 ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በሀገር አቋራጭ ውድድር፤ በጣሊያን ሳን ጆርጂዮ በተካሄደ የ10 ኪሎ ሜትር የሀገር አቋራጭ ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያዊው አትሌት ተስፋዬ ድሪባ 29 ደቂቃ ከ34 ሰከንድ 2ኛ ደረጃን ይዞ በመግባት ውድድሩን አጠናቋል።

በሴቶች 6 ኪሎ ሜትር ሀገር አቋራጭ ውድድር ጌጤ አለማየሁ 19 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ በመግባት 3ኛ ወጥታ ውድድሯን ማጠናቀቋን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።