እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአምስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የቦታና የቀን ለውጥ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26፣ 2010 (ኤፍ. ቢ. ሲ.) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአምስት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ የቦታና የቀን ለውጥ ማድረጉን አስታወቀ።

የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ዘርአብሩክ እንዳሉት፥ “በተለያዩ ምክንያቶች ለውጥ ማድረግ አስፈልጓል' በማለት በክልል ሊካሄዱ የነበሩ ሶሰት ተስተካካይ ጨዎታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም እንዲካሄዱ ተወስኗል።

አቶ ዳንኤል በጨዋታዎቹ ላይ ለተደረገው የቦታና የቀን ለውጥ ምክንያቱን እንዲገልፁ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሊሰጡ አልቻሉም።

በዚሁ መሰረት ወልዋሎ ዓዲ-ግራት ዩኒቨርስቲ ከወልዲያ ከተማ እሁድ ታህሳስ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ሊያደርጉ የነበረውን ጨዋታ ሰኞ ታህሳስ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል ብለዋል።

ፋሲል ከነማ ከመቐሌ ከተማ ጥር 6 ቀን 2010 ዓ.ም ጎንደር ላይ ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄድ ሲሆን፥ ህዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም ወልዲያ ከተማ ከመቐለ ከተማ ወልዲያ ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።

ከቦታ ለውጡ በተጨማሪ በሁለት ጨዋታዎች ላይ ፌዴሬሽኑ የቀን ማስተካከያ አድርጓል።

በዚሁ መሰረት ወልዲያ ከተማ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ታህሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ወልዲያ ላይ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ጥር 24 ቀን 2010 ዓ.ም እዛው ወልዲያ ላይ የሚካሄድ ይሆናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደደቢት ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም መርሀ ግብር ወጥቶለት ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ጥር 13 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄድ ታውቋል።

በተያያዘ ዜና 10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ፣ ቅዳሜ፣ እሁድና ሰኞ እንደሚደረግም ታውቋል።

በመርሃ ግብሩ መሰረት ዛሬ ከቀኑ 11 ሰአት ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማ አባጅፋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ፣ ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌትሪክ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ አስር ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

መርሀ ግብሩ እሁድም ሲቀጥል መከላከያ ከፋሲል ከነማ ከቀኑ ስምንት ሰአት፣ ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ አስር ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የሚጫወቱ ይሆናል።

ክልል ላይ መቀለ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ መቐለ ላይ፣ ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ከተማ ሀዋሳ ላይና አርባ ምንጭ ከተማ ከደደቢት አርባምንጭ ላይ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ የሚካሄዱ ይሆናሉ።

ፕሪሚየር ሊጉን ደደቢት በ19 ነጥብ ሲመራ፥ ጅማ አባ ጅፋር በ14 ነጥብ ሁለተኛ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ13 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ፋሲል ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 12 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ3ኛ እስከ 6ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

 

 

ምንጭ፦ ኢዜአ