በፕሪምየር ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መከላከያና መቀሌ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በዛሬው እለትም ቀጥለው ተካሄደዋል።

በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ስታዲየም የተደረገው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን አርባምንጭ ከተማ አገናኝቷል።

ጨዋታውንም ባለሜዳዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አርባ ምንጭ ከተማን 3ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሙሉ 3 ነጥብ ይዘው ወጥተዋል።

በጨዋታው ላይም ኢብራሂማ ፎፋና በ43ኛው ደቂቃ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ በ83ኛው ደቂቃ እንዲሁም ምንተስኖት አዳነ በ90ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊስን የማሸነፊያ ጎሎች ከመረብ አሳርፈዋል።

የ7ኛ ሳምስት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ክልል ላይም ቀጥለው የተካሄዱ ሲሆን፥ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መከላከያን ያስተናገደበት ጨዋታም ይገኝበታል።

በጨዋታውም መከላከያ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን በሜዳው 1ለ0 በሆነ ውጤት በማሸፍ 3 ነጥብ ይዞ ተመልሷል።

ምንይሉ ወንድሙ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ጋር ያገናኛት ጎል መከላከያን አሸናፊ ማድረግ ችላለች።

ሶዶ ላይ የተካሄደው የወላይታ ድቻ እና የመቀሌ ከተማ ጨዋታ ደግሞ በመቀሌ ከተማ አሸናፊት ተጠናቋል።

መቀሌ ከተማ ጨዋታውን 1ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ የቻለ ሲሆን፥ ጋይሳ አፖንግ በ11ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል መቀሌ ከተማን አሸናፊ አደርጋለች።

አዳማ ላይ የተካሄደው ሌላኛው የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ጨዋታ ደግሞ አዳማ ከተማን ከፋሲል ከነማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አገናኝቷል።

የአዳማ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ ያለ ምንመ ጎል 0ለ0 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በትናንትናው አልት በተካሄዱ የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች፤ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 1ለ0 በሆነ ውጤት ረቷል።

ደደቢት ከሲዳማ ቡና ጋር በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረጉት ጨዋታም በደደቢት 5 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በነገው እለትም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን፥ ጅማ ላይ ጅማ አባ ጅፋርን ከኢትዮጵያ ቡና የሚያገናኘው ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

ወልዲያ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲጫወቱ የወጣው 7ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጨዋታ ደግሞi ወደ ሌላ ጊዜ ተዘዋውሯል።