የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር እና የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊ እና አመራሮች በስፖርታዊ ጨዋነት ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

የጋራ ውይይቱ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የፊታችን እሁድ የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በሰላም እንዲጠናቀቅ እና ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲስተዋልበት ማድረግን ያለመ መሆኑ ተነግሯል።


ውይይቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የደከሙና አሁን አብረው በህይወት ለሌሉት የህሊና ፀሎት በማድረግ ነው የተጀመረው።

በመጪው እሁድ የሚካሄደውን የሁለቱ ክለቦች የፕሪሚየር ሊግ የደርቢ ጨዋታ በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግም ምክክር ተደርጓል።

የሀገሪቱን ትልቁን የደርቢ ጨዋታ ከአደጋ ለመጠበቅ በጋራ መስራት እንደሚገባም ነው በውይይት የተነሳው።

የፀጥታ ሃይሎች በጊዜ መጥተው ከሁለቱም ቡድኖች አስተባባሪዎች ጋር በቅንነት መስራት እንዳለባቸው ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህ ውጭ ክለቦች ደጋፊዎችን ወደ አላስፈላጊ ነገር የሚያነሳሱ ተጫዋቾችን መቅጣት ይኖርባቸዋል የሚል ሀሳብም በውይይቱ ተጠቁሟል።

አስጨፋሪዎች የየራሳቸውን ክለብ ከማሞገስ ባለፈ ከስድብ፣ የሰውን ልጅ ክብር ሊያንቋሽሹ ከሚችሉ ነገሮች የፀዳ ስራ እንዲሰሩም ነው የተመላከተው።

በሁለቱም ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል የሚነሱ የውስጥ ችግሮች በውስጥ መፈታት እንጂ ችግሮቹን ወደ እግር ኳስ ሜዳ ይዞ መምጣት እንደማይገባም ተነግሯል።

በማህበራዊ ድረገፆች በሁለቱም ደጋፊዎች መካከል የሚለቀቁ መረጃዎች ለወጣቱ ደጋፊ ፍቅርን የሚሰብኩ መሆን አለባቸው ተብሏል።

አስተያየት የሰጡ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም መጠጥ ጠጥተው የሚመጡትን የሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች መገሰፅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በዛሬው የውይይት ውሎ የሁለቱም ቡድን አመራሮች በጋራ የሚሰሯቸውን የቤት ስራዎች የወሰዱ ሲሆን፥ ለስታዲየሙ ሰላም መስፈን በቅርበት ያሉት የሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች ሰፊ ሥራ መስራት እንዳለባቸው ከስምምነት ተደርሷል።

በቀጣይ ይህ የውይይት መርሃ ግብር በክልል ከተሞች እንደሚቀጥል ከመድረኩ ተግልጿል።


 

 

በአወቀ አብርሃም