1ኛው የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደር ክለቦችና ተቋማት ሀገር አቋራጭ ውድድር እሁድ በጃንሜዳ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 1ኛው የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደር ክለቦችና ተቋማት ሀገር አቋራጭ ውድድር የፊታችን እሁድ ህዳር 10 2010 ዓ.ም. በጃንሜዳ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሀገር አቋራጭ ውድድሩን በማስመልከተ በዛሬው እለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫውም ውደድሩ የፊታችን እሁድ ህዳር 10 2010 ዓ.ም ከጠዋቱ 1 ሰዓት ጀምሮ በጃንሜዳ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ውድድሩን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዓላማም የክልሎች፣ ከተማ አስተዳደር ክለቦችና ተቋማት በሀገር አቀፍ ውድድር በመሳተፍ ለተተኪ አትሌቶች እድል ለመፍጠርና የሀገር ውስጥ የውድድር ልምድ እንያዳብሩ መሆኑን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

በዚህም መሰረት የፊታችን እሁድ የሚካሄደው የሀገር አቋራጭ ውድድር ላይ አምስት ክልሎች፣ ሁለት የከተማ አስተዳደሮች፣ 13 ክለቦች እና ተቋማት፣ አንዳፋ አትሌቶች እንዲሁም በግል የተመዘገቡ አትሌቶች እንደሚወዳደሩ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ እና የሀረሪ ክልሎች በውድድሩ ላይ ያልተሳተፉ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

አራቱ ክልሎች በውድድሩ ላይ ያልተካፈሉበት ምክንያት ደግሞ የበጀት እጥረት እና ስለ ውድድሩ ወረጃ ቀድሞ ስላልደረሳቸው በቂ ዝግጅት አለማድረግ ነው ተብሏል።

ውድድሩ በሶስት ምድቦች ተከፋፍሎ የሚካሄድ መሆኑን ያስታወቀው ፌዴሬሽኑ፥ የውድድሩ አይነቶችም ፦

በሴቶች

6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች

10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች

በወንዶች

10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ወንዶች

በድብልቅ ሪሌ

8 ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች እና ወንዶች

በውድድሩ ላይ ለሚያሸንፉ አትሌቶችን የዋንጫ፣ የሚዳሊያ እና የገንዘብ ሽልማት እንደሚበረከት ተገልጿል።