የሴካፋ የምድብ ድልድል ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ኬንያ ለምታስተናግደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) የምድብ ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከወቅቱ ቻምፒዮናዋ ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡሩንዲ እና ተጋባዥ ከሆነችው ዚምባቡዌ ጋር ተመድባለች፡፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ሰኞ ህዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም ከቡሩንዲ ጋር 8 ሰዓት ላይ የምታደርግ ይሆናል፡፡

በዋሊያዎቹ ምድብ የሚገኙት ዚምባቡዌዎች ሀገራቸው ፖለቲካዊ ውጥረት ላይ ብትሆንም፥ በሴካፋ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡

 

በምድብ አንድ አዘጋጇ ኬንያ፣ ሊቢያ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ በአንድ ላይ የተደለደሉበት ጠንካራው ምድብ ሆኗል፡፡

ከየምድቡ ሁለት ሃገራት ወደ ግማሽ ፍፃሜው የሚያልፉ ይሆናል፡፡

ጨዋታዎቹ በካካሜጋ፣ ኪሲሙ እና ናኩሩ ስታዲየሞች የሚስተናገዱ ይሆናሉ፡፡

ሁለት ተጋባዥ ሃገራት እና ሰባት የሴካፋ ዞን አባል ሃገራት በውድድሩ ላይ ሲሳተፉ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ እና ሱዳን ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል፡፡

በውድድሩ ታሪክ ኡጋንዳ 13 ጊዜ አሸናፊ በመሆን ክብረ ወሰኑን ስትይዝ፥ ጎረቤት ኬንያ 5 ኢትዮጵያ ደግሞ 4 ጊዜ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

የሴካፋ ዋንጫ በኬንያ ከህዳር 24 ጀምሮ የሚስተናገድ ሲሆን፥ 10 ሀገራት የሚሳተፉበት ይሆናል፡፡

ምድብ አንድ

ኬንያ ፣ ሩዋንዳ ፣ ሊቢያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ዛንዚባር

ምድብ ሁለት

ዩጋንዳ ፣ ዚምባቡዌ ፣ ቡሩንዲ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ደቡብ ሱዳን

የኢትዮጵያ ጨዋታዎች

ሰኞ ህዳር 25 ቀን 2010 ዓ.ም

ቡሩንዲ ከ ኢትዮጵያ (8 ሰዓት)

ዓርብ ህዳር 29 ቀን 2010 ዓ.ም

ደቡብ ሱዳን ከ ኢትዮጵያ (8 ሰዓት)

እሁድ ታህሳስ 1 ቀን 2010 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከ ኡጋንዳ (10 ሰዓት)

ማክሰኞ ታህሳስ 3 ቀን 2010 ዓ.ም

ዚምባቡዌ ከ ኢትዮጵያ (10 ሰዓት)

 

ምንጭ፦ሶከር ኦትዮጵያ