ዴንማርክ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 6 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ዴንማርክ የመጨረሻዋ የአውሮፓ ሃገር በመሆን የ2018ቱን የሩሲያ የአለም ዋንጫ መቀላቀሏን አረጋግጣለች።

ትናንት ምሽት በደብሊን ከሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንድ ጋር የተጫወተችው ዴንማርክ በሰፊ የጎል ልዩነት በማሸነፍ የሩሲያውን የአለም ዋንጫ ተቀላቅላለች።

ጨዋታው 5 ለ 1 ሲጠናቀቅ የቶተንሃም ሆትስፐርሱ አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰን ሃት-ትሪክ መስራት ችሏል።

ዴንማርክ በአለም ዋንጫ ማጣሪያው ጥሩ 2ኛ በመሆን ከጨረሱ ቡድኖች አንደኛዋ ነበረች፤ ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ጨዋታ ያለምንም ጎል ጨዋታቸውን ማጠናቀቃቸው ይታወሳል።

በደርሶ መልስ ማጣሪያው ክሮሺያ፣ ስዊዘርላንድ እና ስዊድን ቀደም ብለው ማለፋቸውን ያረጋገጡ ቡድኖች ናቸው።

በሌላ በኩል ትናንት በተለያዩ ከተሞች የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታዎች ተደርገዋል።

የወቅቱ ጠንካራ ቡድን ጀርመን ፈረንሳይን አስተናግዳ ጨዋታው ሁለት አቻ ተጠናቋል፤ አሌክሳንደር ላካዜት ለሰማያዊዎቹ ሁለቱን ጎሎች ሲያሰቆጥር፥ ለጀርመን ደግሞ ስቲንድል እና ዌርነር አስቆጥረዋል።

ስፔን ከሩሲያ ያደረጉት ጨዋታም 3 አቻ ተጠናቋል፤ ሰርጅዮ ራሞስ ለስፔን ፌድሮ ስሞሎቭ ደግሞ ለሩሲያ በተመሳሳይ ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ጆርዲ አልባ ለስፔን እንዲሁም ሚራንቹክ ለሩሲያ ቀሪዎችን ጎሎች ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

እንግሊዝ ብራዚልን ያስተናገደችበት ጨዋታ ደግሞ ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

አሜሪካ ከፖርቹጋል እንዲሁም ዌልስ ከፓናማም አንድ አቻ የተጠናቀቀ ጨዋታ ነው።

ደቡብ ኮሪያ ከሰርቢያ፣ ኳታር ከአይስላንድ፣ ጋቦን ከቦትስዋናም በተመሳሳይ አቻ ተጠናቀዋል።

ኮሎምቢያ ቻይናን 4 ለ 0፣ ስሎቫኪያ ኖርዌይን እንዲሁም ሃንጋሪ ኮስታሪካን 1 ለ 0 አሸንፈዋል፤ ኦስትሪያ ኡራጋይን 2 ለ 1 ስታሸነፍ ቤልጅየም ደግሞ ጃፓንን 1 ለ 0 ረታለች።

የአፍሪካ ተወካይ የሆነችው ናይጀሪያ ደግሞ ያለ ሜሲ ወደ ሜዳ የገባችውን አርጀንቲናን ማሸነፍ ችላለች።

ኤቨር ባኔጋ እና ሰርጂዮ አጉዌሮ አርጀንቲናን ቀዳሚ ቢያደርጉም፤ ናይጀሪያዎች ከመመራት ተነስተው ማሸነፍ ችለዋል።

ኢሃናቾ፣ ኢዶው አንድ አንድ እንዲሁም አሌክስ ኢዮቢ ሁለት ጎሎችን አስቆጥረው ንስሮቹን ባለድል አድርገዋቸዋል።