አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚነት ሲወዳደሩ የቆዩት አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በይፋ ይቅርታ ጠየቁ።

አቶ ተክለወይኒ ዛሬ በመቐለ ከተማ በሰጡት መግለጫ፥ “ባለፈው ዓርብ እለት የተናገርኩት ንግግር ትክክል አልነበረም” በማለት በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ንግግራቸውም የጉባኤው ተሳታፊዎች ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደጉትን የመቐለ ከተማና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ክለቦችን እንዲሁም የመቐለ ስታዲየምን እንዲጎበኙ ከማሰብ የመነጨ ነው ብለዋል።

በመግለጫቸው ያደረጉት ንግግር ትክክል ባለመሆኑ ይቅርታ እጠይቃለሁ ነው ያሉት።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን እና ሴቶችን በተለይም የመቐለ ከተማ ሴቶችንም ይቅርታ ጠይቀዋል።

ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚነት፥ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትን በመወከል ሲደረግ በነረበረው ምርጫ ውክልናቸው መነሳቱንም ተቀብለዋል።

አቶ ተክለወይኒ በቀጣይ ጊዜያት ከእግር ኳሱ እንደማይርቁም በዛሬው መግለጫ ተናግረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን በተመለከተ በነገው እለት መግለጫ ይሰጣል።

በክብሮም ተስፋይ