ክሮሺያና ስዊዘርላንድ የአለም ዋንጫ ትኬታቸውን ቆርጠዋል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያው የአለም ዋንጫ ለመሳተፍ ጥሩ 2ኛ በመሆን ያጠናቀቁ የአውሮፓ ሃገራት የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርገዋል።

ትናንት ምሽትም ክሮሺያ እና ስዊዘርላንድ የአለም ዋንጫ ትኬት መቁረጣቸውን አረጋግጠዋል።

ወደ ግሪክ ያቀናቸው ክሮሺያ የምሽቱን ጨዋታ ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት አጠናቃለች።

በመጀመሪያው ጨዋታ ዛግሬቭ ላይ ክሮሺያ 4 ለ 1 ማሸነፏ ይታወሳል።

የትናንቱን ውጤት ተከትሎም ክሮሺያ በድምር ውጤት አሸናፊ በመሆን የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን አረጋግጣለች።

በሌላ ጨዋታ በሜዳዋ ሰሜን አየርላንድን ያስተናገደችው ስዊዘርላንድ ጨዋታዋን ባዶ ለባዶ አጠናቃለች።

በመጀመሪያው የቤልፋስት ጨዋታ 1 ለ 0 ያሸነፈችው ስዊዘርላንድ በድምር ውጤት አሸናፊ በመሆን አለም ዋንጫውን ተቀላቅላለች።

ዛሬ ምሽት ደግሞ ስፔንን ተከትላ ምድቧን 2ኛ በመሆን ያጠናቀቀችው ጣሊያን ስዊድንን ትገጥማለች።

በመጀመሪያው ጨዋታ 1 ለ 0 የተሸነፉት ጣሊያኖች ውጤቱን ለመቀልበስ በግዙፉ የሳንሲሮ ስታዲየም ይጫወታሉ።

አንጋፋው ግብ ጠባቂ ጂያንሉጅ ቡፎን 175ኛ ጨዋታውን በሚያደርግበት ግጥሚያ፥ አዙሪዎች ተጫውተን ለማለፍ እንሞክራለን እያሉ ነው።

በዛሬው ጨዋታ ማርኮ ቬራቲ በቅጣት የማይሰለፍ ሲሆን፥ የናፖሊው ሎሬንዞ ኢንሲኜ እርሱን ተክቶ እንደሚገባ ይጠበቃል።

ጣሊያኖች ዛሬ በሳንሲሮ 2 ለ 0 እና ከዚያ በላይ በሆነ ውጤት ማሸነፍ ካልቻሉ፥ ከ60 አመታት በኋላ ከአለም ዋንጫው ውጭ ይሆናሉ።

በሌላ ማጣሪያ ነገ ኮፐንሃገን ላይ ከዴንማርክ ባዶ ለባዶ የተለያዩት ሪፐብሊክ ኦፍ አየርላንዶች የመልስ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።