በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው የ30 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ፅዳት አበጀና በሸንቄ እሙሽ አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በቢሸፍቱ ከተማ በተካሄደው አራተኛው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በወንዶች አትሌት ፅዳት አበጀ እና በሴቶች አትሌት በሸንቄ እሙሽ አሸንፈዋል።

በወንድ አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር የታየበትን ውድድር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አትሌት ፅዳት አበጀ 1 ሰዓት ከ34 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ በመግባት አሸንፏል።

በአንድ ሰከንድ ልዩነት ብቻ ተቀድሞ አትሌት ዘሪቦ ሸኖ ከደቡብ ክልል ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፤ አትሌት ደመቀ ታዬ ከደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ 3ኛ፤ የግል ተወዳዳሪው አትሌት ደጀኔ ከልክል ደግሞ 4ኛ ሆነው ጨርሰዋል።

በሴቶች ደግሞ ደቡብ ክልልን የወከለችው አትሌት በሸንቄ እሙሽ 1 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ቀዳሚ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች።

በግል ተወዳዳሪዋ አትሌት ዝናሽ መኮነን 1 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ከ56 ሰከንድ በመግባት 2ኛ ስትወጣ፥ በተመሳሳይ በግል ተወዳዳሪዋ አትሌት ድሬ ቱኔ 3ኛ እንዲሁም አትሌት አያንቱ ኩምሳ ከኦሮሚያ ፖሊስ 4ኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በሁለቱም ጾታ ውድድሩን በአንደኝነት ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች የ30 ሺህ ብርና የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ሁለተኛ ለወጡ የ22 ሺህ ብርና የብር ሜዳሊያ፣ ሶስተኛ ለወጡት 16 ሺ ብርና የነሐስ ሜዳሊያ የተሸለሙ ሲሆን፤ 4ኛ እና 5ኛ ሆነው ላጠናቀቁት ደግሞ የ13 ሺህ እና የ11 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የፌዴሬሽኑ የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ እንዳሉት፥ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዘጋጅነት በ2000 ዓ.ም የተጀመረው የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በ2003 ዓ.ም በበጀት እጥረት ምክንያት ተቋርጦ ነበር።

አሁን ላይ ፌዴሬሽኑ ከስፖንሰር አድራጊዎች ባገኘው ገቢ ውድድሩን ዳግም ማካሄድ መቻሉን ገለጸው፤ በቀጣይም "ውድድሩ በየዓመቱ ይካሄዳል" ብለዋል።

የጎዳና ላይ ውድድሩ ዓላማ ለአገሪቷ የማራቶን ተወዳዳሪ አትሌቶች የውድድር ዕድል በመፍጠር ልምድ እንዲያገኙ ማድረግና ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሆነ ተገልጿል።

በዛሬው ውድድር ከስምንት ክለቦችና ተቋማት፣ ከሶስት ክልሎችና ከአንድ ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ 234 ወንድና 37 ሴት አትሌቶች ተሳትፈዋል።

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ኢዜአ