የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚጀመርበት ቀን ለ3ኛ ጊዜ ተራዘመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሪሚየር ሊግ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እና የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሚጀመሩበት ቀናት ላይ መሸጋሸግ አድርጓል፡፡

በተራዘመው መርሃ ግብር መሰረት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ይጀመራል ከተባለበት ጥቅምት 18 በአንድ ሳምንት ተራዝሞ ወደ ጥቅምት 25 እና 26 ተሸጋግሯል፡፡ 

ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ መራዘም የክለቦች ጥያቄ እና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዘግይቶ መጠናቀቅን በምክንያትነት አስቀምጧል፡፡

የዘንድሮው የውድድር ዓመት ፕሪሚየር ሊግ የሚጀመርበት ቀን ሲራዘም የአሁኑ ለ3ኛ ጊዜ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ጥቅምት 4 ይጀመራል ቢባልም ወደ ጥቅምት 11 እና ጥቅምት 18 ለሁለት ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል፡፡

ከሊጉ መጀመር በፊት የሚደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ እሁድ ጥቅምት 19 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ መካከል የሚደረገው ይህ መርሃ ግብር፥ በቅድሚያ በደርሶ መልስ መስከረም 25 እና 28 እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም በዝናብ እና በሲቲ ካፕ ምክንያት ወደ ጥቅምት 4 ተሸጋግሮ ነበር፡፡

አሁን ደግሞ በመጪው ጥቅምት 19 ቀን አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡

ሌላው የመርሃ ግብር ለውጥ የተደረገበት የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲሆን፥ ጥቅምት 17 ሊጀመር የታሰበው ውድድር ወደ ጥቅምት 25 ከተዛወረ በኋላ አሁን ደግሞ ወደ ወደ ህዳር 2 ተሸጋግሯል፡፡

 

 

 

 

ምንጭ፦ሶከር ኢትዮጵያ