በቻምፒየንስ ሊጉ ባርሴሎና፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ፒኤስጂ፣ ባየርሙኒክና ጁቬንቱስ አሸንፈዋል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ትናንት ምሽት ከምድብ አንድ እስከ አራት የተደለደሉ ቡድኖች ተጫውተዋል።

በዚህም በምድብ አራት ባርሴሎና በኑካምፕ ኦሎምፒያኮስን አስተናግዶ 3 ለ 1 ረቷል።

ለባርሴሎና ቀዳሚዋን ግብ የኦሎምፒያኮሱ ዲሚትሪስ ኒኮላው በራሱ መረብ ላይ ሲያስቆጥር፥ ሊዮኔል ሜሲ ሁለተኛዋን ሉካስ ዲኜ ሶስተኛዋን ግብ አስቆጥረዋል።

ለተሸናፊው ቡድን ደግሞ በራሱ መረብ ላይ አስቆጥሮ የነበረው ኒኮላው ነው በባርሳዎች መረብ ላይ ብቸኛዋን ግብ ያሳረፈው።

ጄራርድ ፒኬ በቀይ በተሰናበተበት ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ በአውሮፓ መድረክ ጨዋታዎች ያስቆጠራቸውን ግቦች 100 አድርሷል።

በተመሳሳይ ምድብ የሚገኘው ጁቬንቱስ በሜዳው ስፖርቲንግ ሊዝበንን አስተናግዶ 2 ለ 1 ሲረታ ሚራለም ፒያኒች እና ማሪዮ ማንዙኪች የድል ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ለስፖርቲንግ አሌክስ ሳንድሮ በራሱ መረብ ላይ አግብቷል።

ምድብ አንድ ላይ ከሜዳው ውጭ ቤኔፊካን የገጠመው ማንቼስተር ዩናይትድ በማርከስ ራሽፎርድ ብቸኛ ግብ 1 ለ 0 አሸንፎ ተመልሷል።

በዚሁ ምድብ ባዜል ሴ ኤስ ኬ ኤ ሞስኮን 2 ለባዶ ረቷል፤ ታውላንት ዣካ እና አበርሊኒ ሁለቱን ግቦች ከመረብ ያዋሃዱ ተጫዋቾች ናቸው።

በምድብ ሁለት ደግሞ ፓሪስ ሴንት ጀርሜይን (ፒኤስጂ) ደግሞ አንደርሌክትን 4 ለ 0 ያሸነፈ ሲሆን፥ ኪሊያን ምባፔ ቀዳሚዋን፣ ኤዲንሰን ካቫኒ ሁለተኛዋን፣ ኔይማር ጁኒየር ሶስተኛዋን እና የመጨረሻዋን ግብ አንሄል ዲማሪያ ከመረብ አዋህደዋል።

በምድቡ ሌላ ጨዋታ ባየር ሙኒክ ሴልቲክን 3 ለ 0 ሲረታ፥ ቶማስ ሙለር፣ ጆሹዋ ኪሚች፣ ማትስ ሁመልስ የግብቹ ባለቤቶች ናቸው።

ምድብ ሶስት ቼልሲ በስታምፎርድ ብሪጅ ሮማን ባስተናገደበት ጨዋታ 3 ለ 3 አቻ ተለያይቷል።

ለሰማያዊዎቹ ኤደን ሃዛርድ ሁለት ዴቪድ ሊዩዝ አንድ ሲያስገቡ፥ ለሮማዎች ደግሞ ሁለቱን ኤዲን ዤኮ አንዷን ደግሞ አሌክሳንደር ኮላሮቭ ናቸው ያስቆጠሩት።

በምድቡ ሌላ ጨዋታ ቃራባግ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ባዶ ለባዶ አቻ ተለያይተዋል።

በቻምፒየንስ ሊጉ የየምድቦቹ ሶስተኛ ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን፥ በምድብ አንድ ማንቼስተር ዩናትድ በ9፣ ባዜል በ6፣ ሲኤስ ኬ ኤ ሞስኮ በ3 እና ቤኔፊካ በ0 ነጥብ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ምድብ ሁለትን ፒ ኤስ ጂ በ9 ነጥብ ሲመራ ባየርሙኒክ 6፣ ሴልቲክ 3 እና አንድርሌክት 0 ነጥብ በመያዝ ከ3ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ተቀምጠዋል።

ቼልሲ በ7 ነጥብ ምድብ ሶስትን እየመራ ሲሆን፥ ሮማ በ5 ሲከተል አትሌቲኮ ማድሪድ በ2 እና ቃራባግ በ1 ነጥብ ግርጌ ላይ ናቸው።

ባርሴሎና ምድብ አራትን በ9 ነጥቦች እየመራ ነው።

ጁቬንቱስ በ6፣ ስፖርቲንግ ሊዝበን በ3 ነጥብ 2ኛ እና 3ኛ ደረጃን ሲይዙ፥ ኦሎምፒያኮስ በሶስት ጨዋታዎች ሽንፈትን በማስተናገዱ ምንም ነጥብ የለውም።

ምድብ አምስት ላይ ሊቨርፑል እና ስፓርታክ ሞስኮ በተመሳሳይ 5 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፥ ሴቪያ በ4 ነጥብ 3ኛ ሲሆን ኤንኬ ማሪቦር ደግሞ በ1 ነጥብ መጨረሻ ላይ ይገኛል።

የፔፔ ጋርዲዮላው ማንቸስተር ሲቲ ምድብ ስድስትን በ9 ነጥቦች ይመራል።

ሻክታር ዶኔስክ በ6፣ ናፖሊ በ3፣ ፌይኖርድ በ0 ነጥብ ተከታዮቹ ደረጃዎች ላይ ይገኛሉ።

ምድብ ሰባትን ቤሲክታሽ በ9 ነጥብ በአንደኝነት ሲመራ፣ አር ቢ ሌይፕዚግ በ4፣ ኤፍ ሲ ፖርቶ በ3፣ ሞናኮ በ1 ነጥብ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

የለንደኑ ቶተንሃም ሆትስፐር በያዝነው ሳምንት በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ሪያል ማድሪድን ገጥሞ 1 ለ 1 በመለያየቱ፥ ምድብ ስምንትን በ7 ነጥቦች ሲመራ፣ ማድሪድ በተመሳሳይ 7 ነጥብ ይከተላል።

ቦሩሲያ ዶርትሙንድ እና አፖል ኒኮሲያ ተመሳሳይ 1 ነጥብ ቢይዙም፥ ዶርትሙንድ ባለበት የግብ እዳ የተሻለ በመሆኑ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።

 

 

በምህረት አንዱዓለም