ግብጽ ከ28 አመት በኋላ ወደ አለም ዋንጫው ተመልሳለች

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 29 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ግብጽ በሩሲያው የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን በማረጋጥ ሁለተኛዋ አፍሪካዊት ሃገር ሆናለች።

በምድብ አምስት ትናንት ምሽት በአሌክሳንድሪያ ከኮንጎ ጋር የተጫወቱት ፈርኦኖች ከ28 አመታት በኋላ ወደ አለም ዋንጫው ተመልሰዋል።

በቦርግ አል ዓረብ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ መሃመድ ሳላህ ፈርኦኖቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር።

በጨዋታው መጠናቀቂያ አካባቢም ኮንጎዎች በአርኖልድ ቦካ ሞቶው ጎል አቻ መሆን ችለዋል።

የምሽቱ ጀግና የነበረው መሃመድ ሳላህ ሁለተኛዋን ጎል በፍጹም ቅጣት ምት በ95ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠር ችሏል።

ውጤቱን ተከትሎም ግብጾች ከጣሊያኑ የ19 90 የአለም ዋንጫ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በውጤቱ የተደሰቱ ግብጻውያንም በመላ ሃገሪቱ በሚገኙ አደባባዮች በመሰባሰብ ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛል።

ለፖለቲካ ተቃውሞ የሚወጡበት የታህሪር አደባባይም በደስታ የሰከሩ ግብጻውያንን አስተናግዷል።

በአህጉራዊው ውድድር ደማቅ ታሪክ ያላቸው ግብጾች በአለም ዋንጫው መድረክ ግን በተቃራኒው ይጓዛሉ።

በምድቡ ከትናንት በስቲያ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ዩጋንዳ ከጋና ጋር ተጫውታ አቻ መለያየቷ ይታወሳል።

ግብጽ ትናንት ማሸነፏን ተከትሎም ምድቡን በአራት ነጥብ ልዩነት ስትመራ፥ የቀረው የአንድ ጨዋታ መርሃ ግብር በመሆኑ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን እንድታረጋግጥ አስችሏታል።

የብሄራዊ ቡድኑ ግብ ጠባቂ ኤሳም ኤል ሃዳሪም በመጭው ሰኔ ወር በሚደረገው የአለም ዋንጫ ለቡድኑ ከተሰለፈ በአለም ዋንጫ ታሪክ አዛውንቱ ግብ ጠባቂ ይሆናል።

በወቅቱ 45 አመቱን የሚይዘው ኤል ሃዳሪ፥ በሩሲያው የአለም ዋንጫ ከተሳተፈ ከዚህ ቀደም በኮሎምቢያዊው ግብ ጠባቂ ፋሪድ ሞንድራጎን የተያዘውን ክብረ ወሰን ማሻሻል ይችላል።

ባለፈው የአለም ዋንጫ ሃገሩን የወከለው ሞንድራጎን በ43 አመቱ ክብረ ወሰኑን ይዞት ቆይቷል።