በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ደደቢት ሲሸነፍ ቡና አቻ ተለያይቷል

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 28 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ የተጀመረው የ2010 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሁለት ጨዋታዎች ተደርጎበታል።

ከቀትር በኋላ በተደረገ ጨዋታ ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደው አዲስ አበባ ከተማ ከደደቢት ተጫውተዋል።

ጨዋታውን አዲስ አበባ ከተማ ከእረፍት መልስ ባስቆጠራት ጎል 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

አመሻሽ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና የፕሪሚየር ሊጉን እንግዳ ጅማ አባ ጅፋርን አስተናግዷል።

በርካታ ደጋፊዎች ስታዲየም ገብተው የተከታተሉት ጨዋታ ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

በውድድሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ደደቢት፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መከላከያ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ አዲስ አበባ ከተማና አዳማ ከተማ ተሳታፊ ናቸው።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ አምና የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል።