ፊፋ በቼልሲና ማንቸስተር ሲቲ ላይ ምርመራ እያካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ፊፋ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ከሆኑ ተጫዋቾች ዝውውር ጋር በተገናኘ በቼልሲና ማንቸስተር ሲቲ ላይ ምርመራ እያደረገ ነው።

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌደሬሽን በቼልሲ ላይ ምርመራ ለማድረግ ሲያቅድ የአሁኑ የሶስተኛ ጊዜው ሲሆን፥ ሰማያዊዎቹ በፈረንጆቹ 2009 ለሁለት ዓመታት ያህል ተጫዋቾችን እንዳያስፈርሙ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር።

በሳለፍነው ግንቦት ወር የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የስልጠና ፕሮጀክት ተጫዋቾችን ከማስፈረም ጋር በተያያዘ ቼልሲን 300 ሺህ ፓውንድ እንደቀጣው ይታወሳል።

ፊፋ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ተጫዋቾችን ከጉልበት ብዝበዛ ጋር በተገናኘ ክለቦች እንዳያስፈርሙ የሚከለክል ህግ አለው።

በቼልሲ እና በማንቸስተር ሲቲ ላይ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን አረጋግጧል።

ሲቲ ስለ ምርመራው መረጃ እንደሌለው የገለፀ ሲሆን ምንም ዓይነት የህግ ጥሰት እንዳልፈፀመ ጠቁሟል።

ቼልሲ በበኩሉ ተጫዋቾችን ሲመለምልና ሲያስፈርም የፊፋን ደንቦች ተከትሎ መሆኑን ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።

ክለቡ በፈረንጆቹ 2009 ጋብሪኤል ካኩታን ከፈረንሳዩ ሌንስ ክለብ ውል አፍርሶ በማስፈረሙ፥ ለሁለት ዓመታት ተጫዋች እንዳያስፈርም ታግዶ የነበረ ቢሆንም ይግባኝ ጠይቆ እገዳው ተነስቶለታል።

ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመትም በ2014 በርትራንድ ትራኦሬን ከቡርኪናፋሶ ክለብ ያስፈረመበት ሂደት ምርመራ ተደርጎበታል።

ሲቲ ደግሞ ለሌላ ክለብ የፈረሙ ሁለት ታዳጊዎችን ለማስፈረም ሞክሯል በሚል ክስ ቀርቦበታል።

ክልቡ በ2016 ከአርጀንቲናው ቬለዝ ሳርስፊልድ ክለብ የ16 ዓመቱን ቤንጃሚን ጋሬ በማስፈረሙ፥ የቀረበበትን ክስ ለዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ማቅረቡ ይታወቃል።

ፊፋ ተጫዋቹን በዜግነቱ ምክንያት ለማስፈረም እንዳልተፈቀደለት እና ተጫዋቹ የጣሊያን ፓስፖርት ይዞ እንደነበር በማስረዳት ሲቲ ያቀረበውን መቃወሚያ ውድቅ አድርጓል።

ፌዴሬሽኑ ከ18 ዓመት በታች እድሜ ያላቸው ተጫዋቾችን ከአንደ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር ክለብ ለማስፈረም የሚቻለው የተጫዋቹ ወላጆች አዲሱ ክለብ በሚገኝበት ሀገር ስፖርታዊ ባልሆነ ምክንያት የሄደው የሚኖሩ መሆን አለባቸው ይላል።

ከዚህ ውጭ ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ ህብረት ወይም በአውሮፓ የኢኮኖሚ ቀጠና ውስጥ የሚገኙና እድሜያቸውም ከ16 እስከ 18 ዓመት መሆን አለበት የሚል ደንብ አለው።

ክለቡ ተጫዋቹን ሲያዘዋውር ከትምህርት፣ የኑሮ ሁኔታ እና ሌሎች ድጋፎች ጋር በተገናኘ ማሟላት የሚጠበቅበት መስፈርቶችም እንዳሉ ተነግሯል።

ተጫዋቾች ከክለቡ በ100 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚኖሩ መሆን ይገባቸዋል የሚል ድንጋጌም አለ።

ቸልሲ እና ማንቸስተር ሲቲ አሁን የሚቀርብባቸውን የወንጀል ምርምራ የተቃወሙ ሲሆን፥ በእንግሊዝ ምርጥ የሚባሉ የታዳጊ ተጫዋች ቡድን እንዳላቸውም አንስተዋል።