በፊፋ ወርሃዊ ደረጃ ኢትዮጵያ 24 ደረጃዎችን ዝቅ ብላለች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ወርሃዊው የሃገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 24 ደረጃዎችን ዝቅ ብላለች።

ፊፋ ባወጣው የወሩ ደረጃ ጀርመን አንድ ደረጃ በማሻሻል አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ብራዚል ካለፈው ወር መሪነቷ አንድ ደረጃ በመቀነስ ሁለተኛ ላይ ስትቀመጥ፥ ፖርቹጋል በሃምሌ ወር ከነበረችበት ሶስት ደረጃዎችን በማሻሻል ወደ ሶስተኛ ደረጃ ከፍ ብላለች።

ኢትዮጵያ በሃምሌ ወር ከነበረችበት 120ኛ ደረጃ አሁን ወደ 144ኛ ወርዳለች።

ከአፍሪካ ሀገራት ደግሞ 44ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ከአፍሪካ ግብፅ ቀዳሚ ስትሆን ከዓለም ደግሞ አምስት ደዋዎችን አሽቆልቁላ 30ኛ ደረጃን ይዛለች፤ ቱኒዚያ ሶስት ደረጃዎችን በማሻሻል ከዓለም 31ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ግብፅን ተከትላ 2ኛ ሆናለች።

ሴኔጋል ደግሞ ሁለት ደረጃዎችን በመቀነስ ከዓለም 33ኛ ከአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በወሩ ኬፕ ቨርዲ 47፣ ሉክሰምበርግ 35 መቄዶኒያ 32 እንዲሁም ቆጵሮስ 24 ደረጃዎችን በማሻሻል የተሻለ ወርሃዊ ደረጃ አግኝተዋል።

በአንጻሩ ጓቲማላ 31 እና ኢትዮጵያ 24 ደረጃዎችን በማሽቆልቆል የከፋ ውጤት አስመዝግበዋል።

አንጉሊያ፣ ባህማስ፣ ኤርትራ፣ ጅብራልተር፣ ሶማሊያ እና ቶንጋ ደግሞ አሁንም ያለምንም ነጥብ በደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።