በሻምፒየንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ሲቲና ቶተንሃም ሲያሸንፉ ሊቨርፑል አቻ ወጥቷል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታ ሁለተኛ ቀን ከምድብ አምስት እስከ ስምንት የተደለደሉ ቡድኖች ያደረጉትን ጨዋታ አስተናግዷል።

በቡድን ስምንት የሚገኘው ሪያል ማድሪድ በሳንቲያጎ ቤርናቢዮ ተጋጣሚያውን አፖል ኒኮሲያን 3 ለ 0 በረታበት ጨዋታ ክርሰቲያኖ ሮናልዶ ከቅጣት መልስ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል።

የዚዳንን ቡድን ቀሪ የማሸነፊያ ግብ ሰርጂዮ ራሞስ አስቆጥሯል።

በተመሳሳይ ምድብ የሚገኘው የእንግሊዙ ቶተንሃም ሆትስፐር የጀርመኑን ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በዌምብሌይ አስተናግዶ 3 ለ1 አሸንፏል።

ለቶተንሃም ሃሪ ኬን ሁለት ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ ሰን ሄንግ ሚን ቀሪዋን ግብ በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አሳርፏል።

ያርሞሌንኮ ለዶርትሙንድ በባዶ ከመሸነፍ ያዳነችውን አንድ ግብ በስሙ አስመዝግቧል።

ምድብ አምስት ላይ የተደለደሉት ሊቨርፑል ከሲቪያ 2 ለ2 አቻ ሲለያዩ፥ ከፈረንጆቹ 2014 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሻምፒየንስ ሊጉ ለተሳተፉት ቀዮቹ ሮቤርቶ ፊርሚኒዮና ሞሃመድ ሳላህ ግቦቹን ሲያስቆጥሩ ለሲቪያ ቤን ዬዴርና ጃኩዪን ቾሬአ አቻ አድርገዋል።

በዚህ ምድብ ማሪቦርና ስፓርታክ ሞስኮ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ተጠናቋል።

ምድብ ስድስት ውስጥ የሚገኘው ማንቸስተር ሲቲ ፌይኖርድን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲረታ ጆን ስቶንስ ሁለት፣ ሰርጂዮ አጉዌሮና ጋብሬል ሄሱስ ቀሪ አንድ አንድ ግቦችን በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ አስገብተዋል።

በተመሳሳይ ምድብ የሚገኘው የጣሊያኑ ናፖሊ ወደ ዩክሬን አቅንቶ በሻካታር ዶኔስከ 2ለ1 ተረቷል።

በድልድሉ ሰባተኛው ምድብ ላይ የሚገኘው የቱርኩ ቤሺክታሽ የፖርቹጋሉን ፖርቶ ከሜዳው ውጭ 3 ለ 1 ሲያሸንፍ፥ ሞናኮ እና አር ቢ ላይፕዚግ በአንድ አቻ ተለያይተዋል።