በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ባርሴሎና ዩቬንቱስን ሲያሸንፍ ፒ.ኤስ.ጂና ቸልሲ በሰፊ የግብ ልዩነት ድል ቀንቷቸዋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት ምሽት በተካሄደው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ባርሴሎና ዩቬንቱስን ሲያሸንፍ ፒ ኤስ ጂ እና ቸልሲም በከፍተኛ ጎል ልዩነት ድል አድርገዋል።

ከ78 ሺህ በላይ ተመልካች በተከታተለው የካምፕ ኑ ጨዋታ አርጀንቲናዊው ሊዮኔል ሜሲ ደምቆ አምሽቷል።

በሳምንቱ የላሊጋ ጨዋታ ሀትሪክ የሰራው ሜሲ ምሽት 2 ኳሶችን ከመረብ ያሳረፈ ሲሆን፥ ክሮሺያዊው ራክቲች ቀሪዋን በስሙ አስመዝግቧል።

በዚህ ምድብ ሌላኛው ፍልሚያ ስፖርቲንግ ሊዝበን ወደ ግሪክ አቅንቶ ኦሎምፒያኮስን 3ለ2 ረቶ ተመልሷል።

በምድብ አንድ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ በኦልትራፎርድ ባዜልን 3ለ0 አሸንፏል።

የሆዜ ሞሪኒሆ ተመራጭ ማርዋን ፌይላኒ፣ በምርጥ አቋም ላይ የሚገኘው ሮሜሉ ሉካኩ እና ማርከስ ራሽፎርድ ጎሎቹን አስቆጥረዋል።

ቤኒፊካ በሜዳው በሩሲያው ሲ ኤስ ኬ ኤ ሞስኮ 2ለ1 ተሸንፏል።

በቡንደስ ሊጋው በሆፍናይም 2ለ0 የተረታው ባየር ሙኒክ በአሊያንዝ አሬና የቤልጄሙ አንደርሌክትን 3ለ0 ሲረታ ሎዋንዶውስኪ፣ ቲያጎ አልካንትራ እና ጆሽዋ ኪሚችበ የጎሎቹ ባለቤቶች ሆነዋል።

ወደ ስኮትላድ ሴልቲክ ያመራው ፒ ኤስ ጂ በሴልቲክ ፓርክ በጎል ተንበሽብሾ ተመልሷል።

ኔይማር ደምቆ ባመሸበት ጨዋታ አንድ ጎል አስቆጥሮ ጎል የሆነ ኳስ ሲያቀብል፣ ኪሊን ምባፔ አንድ፣ ኤዲንሰን ካቫኒ 2 ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል።

ሚካኤል ለስቲግ ሌላኛውን ጎል በራሱ መረብ ላይ አሳርፏል።

የአንቶኒ ኮንቴው ቸልሲ በአዘርባጃኑ ካራባህ መረብ ላይ 6 ኳሶችን አሳርፏል።

ፔድሮ ሮድሪጌዝ፣ ዳቪድ ዛፓኮስታ፣ ሴዛር አዝፕሊኩዌታ፣ ባካያኮ እና ሚቺ ባሽዋዬ አንዳንድ ጎሎችን ሲስቆጥሩ ሜድቬዴቭ በራሱ መረብ ላይ ቀሪዋን አክሏል።

በምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ ሮማ እና አትሌቲኮ ማድሪድ 0ለ0 ተለያይተዋል።

በቻምፒየን ሊጉ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽትም ቀጥለው ይደረጋሉ።

በምድብ 5 ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድሮድ የስፔኑ ሴቪያን የሚስተናግድበት ጨዋታ ከፍተኛ ግምት አግኝቷል።

ሊቨርፑል ከ4ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ የማንችስተር ሲቲ የ5ለ0 ሽንፈት በኋላ ነው የዛሬውን ጨዋታ የሚያደርገው።

ጀርመናዊው ሎሪስ ካሪየስ ሲሞን ሚኞሌትን ተክቶ የቀዮቹን ግብ የሚጠብቅ ሲሆን፥ ፊሊፔ ኮቲኒሆ በጨዋታው እንደሚሰለፍ አሰልጣኙ የርገን ክሎፕ ማረጋገጫ አልሰጡም፡፡

በሳምንቱ ከባድ ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተወገደው ሴኔጋላዊው ሳይዶ ማኔ በዛሬው ጨዋታ ይሰለፋል።

በላሊጋው ምርጥ አቋም እያሳየ የሚገኘው የኤድዋርዶ ቤሪዞው ሴቪያ ከአመት በፊት በዩሮፓ ሊግ ፍጻሜ የመርሲሳይዱን ክለብ በአሳማኝ ሁኔታ አሸንፎ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል፡፡

በዚህ ምድብ ሌላኛው ጨዋታ የስሎቬኒያው ማሪቦር ስፓርታክ ሞስኮን ያስተናግዳል፡፡

የፔፕ ጋርዲዮላው ማንችስተር ሲቲ በምድብ 6 የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከፌይኖርድ ጋር በማድረግ ይጀምራል፡፡

የሰርጂዮ ኩን አጉዌሮ እና ሄሱስ ናቫስ ጥምረት በሲቲ በኩል እየተወደሰ ይገኛል፡፡

የዛሬው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙበት ነው፡፡

የፖርቱጋሉ ፖርቶ ከቱርኩ ቤሺክታሽ ፣ የጀርመኑ አር ቢ ላይብዚሽ ከሞናኮ በምድብ 7 የሚደረጉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

በመጨረሻው ምድብ በላሊጋው ያልተጠበቀ አቋም ያሳየው ሻምፒዮኑ ሪያል ማድሪድ የቆጵሮሱ አፖይል ኒኮሲያን በቤርናባው ያስተናግዳል፡፡

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከላሊጋው የጨዋታ ቅጣት እረፍት በኋላ ነጩን መለያ ለብሶ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

እንዲሁም የእንግሊዙ ቶትንሀም ሆትስፐር ከጀርመኑ ቦርሲያ ዶርትመንድ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታም ዛሬ ምሽት ከሚጠበቁ ጨዋታዎች ውስጥ ነው።

ሁሉም ጨዋታዎች ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ይጀምራሉ።

በዘላለም ተፈሪ