በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለተሳተፈው ቡድን የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሀዋሳ ከተማ የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ተበረከተ።

ትናንት ምሽት በተካሄደው የእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት በሻምፒዮናው የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ተበርክቶላቸዋል።

በእውቅናና የማበረታቻ ሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአትሌቶቹ ሽልማቱን አበርክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ባስተላለፉት ምልእክትም፥ በ16ኛው አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍ ወርቅ ያመጡም ያላመጡም አትሌቶች የኢትዮጵያ ስም እንዲጠራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ብለዋል።

አትሌቶቹ በለንደን በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ላመጡት ውጤትም ምስጋና አቅርበዋል።

ስፖርት አመራር ይጠይቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፥ የስፖርት ማህበራትን የሚመሩ አካላት በስፖርቱ ያለፉ እና እውቀቱ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል በማለት የእነ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን ወደ አመራርነት መምጣት በማሳያነት አንስተዋል።

“በመሆኑም በቀጣይ የስፖርት ፌዴሬሽኖችን ለመምራት በክልሎች የሚወከሉ አካላት ሙያው እና እውቀቱ ያላቸው እንዲሆኑ ትግል ልናደርግ ይገባል” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አያይዘውም፥ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ለጤናማ አኗኗር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ የስፖርት እንቅስቃሴ በሀገራችን ባህል እንዲሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ትልቅ ሚና ሊጫወቱ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ትምህርት ቤቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ሊገነቡ እና ሊያዘጋጁ እንደሚገባና በየደረጃው የሚገኘው አመራር ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው፥ ኢትዮጵያ ከላት አቅምና ድል አኳያ የተሰራው ስራ እና የተገኘው ውጤት በቂ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።
በቀጣይ የሉትን እድሎች በመጠቀም እና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የላቀ ውጤት ለማምጣት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

london_1_2.jpg

በ16ኛው የለንደን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች በአዲስ አበባ ከተማ የቤት መስሪያ ቦታ የተበረከተላቸው ሲሆን፥ አትሌት አልማዝ አያና 500 ካሬ ሜትር እንዲሁም ሙክታር እድሪስ 400 ካሬ ሜትር መሬት ተሰጥቷቸዋል።

የብር ሜዳሊያ ላስገኙ አትሌቶች 75 ሺህ ብር፣ አትሌት ዮሚፍ ቀጀልቻ ልዩ ተሽላሚ በመሆን 50 ሺህ ብር፣ ዲፕሎማ ላመጡ ለእያንዳንዳቸው 20 ሺህ ብር እንዲሆም ለተሳታፊ አትሌቶች የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቷል።

የተሻለ ውጤት ያስገኙ አሰልጣኞች ከ60 ሺህ እስከ 20 ሺህ የተሸለሙ ሲሆን፥ የአትሌት አልማዝ አያና አሰልጣኝና ባለቤት ልዩ ተሸላሚ በመባል 60 ሺህ ብር ተሸልሟል።

በሽልማቱ በአጠቃላይ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መሆኑን ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በለንደን አስተናጋጅነት የተጀካሄደ ሲሆን፥ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችው ኢትዮጵያም ሁለት የወርቅ እና ሶስት የብር ሜዳሊያዎች በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ውድድሩን ማጠናቀቋ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ኢትዮጵያ ከዓለም 7ኛ ደረጃን ስትይዝ፤ ከአፍሪካ ደግሞ 3ኛ ደረጃን ይዛ ነበር ያጠናቀቀችው።

በሙለታ መንገሻ