ታዋቂ አትሌቶችና የእግር ኳስ ክለቦች የተሳተፉበት ስፖርታዊ ውድድሮች ተካሄዱ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ2010 አዲስ ዓመት አቀባበል አካል የሆነ የአትሌቲክስ እና የእግር ኳስ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።

“መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የ2010 አዲስ ዓመት አቀባበል በማስመልከት ነው ስፖርታዊ ውድድሮቹ የተካሄዱት።

በዛሬው እለት ከተካሄዱት ውደድሮች ውስጥም ታዋቂ እና አንጋፋ የሀገራችን አትሌቶች የተሳተፉበት የ1 ሺህ 500 ሜትር የወንዶች እና የሴቶች የሩጫ ውድድር ይገኝበታል።

በወንዶች በተደረገው ውድድርም አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ በአንደኝነት ሲያጠናቅቅ፤ አትሌት ገዛኸኝ አበራ 2ኛ እንዲሁም አትሌት አሰፋ መዝገቡ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

sport_kefeta.jpg

በሴቶች በተደረገው ውድድር ደግሞ አትሌት ቁጥሬ ዱለቻ 1ኛ በመውጣት ውድድሩን ስታጠናቅቅ፤ አትሌት ውርቅነሽ ኪዳኔ 2ኛ እንዲሁም አትሌት ጌጤ ዋሚ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።

sport_kefeta_2.jpg

በተመሳሳይ በአንጋፋዎቹ የእግር ኳስ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከልም የእግር ኳስ ውድድር ተካሂዷል።

sport_kefeta_3.jpg

በዚህም ኢትዮጵያ ቡና 2ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የተዘጋጀውን የክብር ዋንጫ መውሰድ ችሏል።

በተጨማሪም በቦክስ፣ ጅምናስቲክ እና በሌሎችም ስፖርቶች ውድድሮች ተካሂደዋል።

ውድድሮቹንም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሌሎች የስፖርት ማህበራት አዘጋጅነት ነው የተካሄዱት።