ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበት ሩጫና የታዋቂ ክለቦች የእግር ኳስ ጨዋታ ቅዳሜ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የ2010 ዓዲስ ዓመት አከባበር አካል የሆኑ የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖች የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚካሄዱ ተገለፀ።

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ሌሎች የስፖርት ማህበራት የአዲሱን ዓመት አቀባበል በማስመልከት በዛሬው እለት በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

“መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን የ2010 አዲስ ዓመት አቀባበል በማስመልከትም፥ ቅዳሜ ጳጉሜ 4 ቀን 2009 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ስታዲየም የተለያዩ ስፖርታዊ ክንውኖች እንደሚካሄዱ ተገልጿል።

በመግለጫው፥ አዲሱን ዓመት በአዲስ አበባ ስታዲየም ከህብረተሰቡ ጋር በታላቅ ድምቀት ለመቀበልና ለማክበር፥ በአትሌቲክስ በ1 ሺህ 500 ሜትር በሁለቱም ጾታ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ተነግሯል።

በውድድሩ ላይ አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ እና አትሌት ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ አትሌቶች የሚሮጡ መሆኑም ተገልጿል።

እንዲሁም በእለቱ አንጋፋዎቹ የእግር ኳስ ክለቦች ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ የሚጫወቱ መሆኑም ታውቋል።

በተጨማሪም በቦክስ፣ ጅምናስቲክ እና በሌሎችም ስፖርቶች ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚደረጉ በጋዜጣዊ መግለጫው ይፋ ተደርጓል፡፡

የወጣቶችና ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ ርሰቱ ይርዳው፥ በመጪዉ ዓመት የስፖርት ልማትን ለማፋጠንና ለህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ባለፉት የተገኙትን ስኬቶች ይበልጥ በማጠናከር የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

“መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ” በመሆኑም ለሀገሪቱ ልማት ስፖርት ጤናማ ዜጋን በማፍራት በኩል ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት፥ ለዚህም ጠንክረን እንሰራለን ያሉት ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውንም አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፥ ለመላው የኦሊምፒክ ቤተሰብና የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

ዶክተር አሸብር፥ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ከሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት ጋር በሀገሪቱ ስፖርት እድገት እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ ለማጠናከርና የሀገሪቱን የስፖርት ህዳሴ እንዲረጋገጥ ለማስቻል፥ ከምንጊዜውም በተሻለ በመጪው ዓመት ይሰራል ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን በሻ ለውድድሮቹ አስፈላጊ ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።