ፊፋ የደቡብ አፍሪካና የሴኔጋል የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በድጋሚ እንዲካሄድ ወሰነ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 2፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ፊፋ) በደቡብ አፍሪካና በሴኔጋል መካከል የነበረው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንደገና እንዲካሄድ ውሳኔ ሰጥቷል።

ባለፈው አመት ህዳር ወር ላይ የተደረገውን ጨዋታ በመሃል ዳኝነት የመሩት ጋናዊ ዳኛ ጆሴፍ ሌምቴይ፥ ከዚህ በኋላ በማንኛውም እግር ኳስ የዳኝነት ስራ ላይ እንዳይሳተፉም የህይወት ዘመን እገዳ ጥሎባቸዋል።

ጆሴፍ ሌምቴይ በዚያ ጨዋታ ላይ ደቡብ አፍሪካ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ሴኔጋልን እንድታሸንፍ የሰጡት የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢ አይደለም በሚል ነው ፊፋ ቅጣቱን በዳኛው ላይ ያሳለፈው።

refrree.jpg

በጨዋታው ላይ ዳኛው የፍፁም ቅጣት ምቱን የሰጡት ሴኔጋላዊው የናፖሊው ተከላካይ ካሊዱ ኩሊባሊ ኳስ በእጁ ነክቷል በሚል ነበር።

ሆኖም በምልሰት ምልከታ ኳሷ የሰኔጋሉን ተጫዋች ጉልበት እንጅ እጁን አለመንካቷ ተረጋገጧል።

ፊፋም ደቡብ አፍሪካ ያሸነፈችበትን የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ውጤት ሰርዞ፥ በመጪው ህዳር ወር በሚካሄዱ የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ላይ እንዲጫዎቱ አዟል።

ጋናዊው ዳኛ ሌምቴይ በህይወት ዘመናቸው ጨዋታ እንዳይመሩ ውሳኔ የተላለፈባቸው ባሳለፍነው መጋቢት ወር ላይ ቢሆንም፥ ዓለም አቀፉ የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት ትናንት ውሳኔውን አፅንቶታል።

ፊፋ ጉዳዩን አጣርቶ ውሳኔ ላይ የደረሰውና በዳኛው ላይ ቅጣት ያሳለፈው፥ የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ነው።

ሴኔጋልና ደቡብ አፍሪካ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያው በምድብ አራት ስር አንድ ምድብ ተደልድለዋል።

ቡርኪና ፋሶንና ኬፕ ቨርዲን ተከትለው በቅደም ተከተል 3ኛና 4ኘ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በሩሲያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የ2018 የዓለም ዋንጫ በአፍሪካ ዞን የምድብ መሪ ቡድኖች ብቻ ይሳተፋሉ።