ዋይኒ ሩኒ ራሱን ከብሄራዊ ቡድን አገለለ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 17 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድንና የማንቼስተር ዩናይትድ የምንጊዜም ከፍተኛ ጎል አግቢው ዋይኒ ሩኒ ራሱን ከብሄራዊ ቡድኑ ማግለሉን አስታወቀ።

በአዲሱ የውድድር ዘመን ማንቼስተርን ለቆ ወደ ልጅነት ክለቡ ኤቨርተን ያመራው ሩኒ ከብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጋሬዝ ሳውዝጌት ጋር ባደረገው የስልክ ቆይታ ከብሄራዊ ቡድኑ ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።

በፕሪሚየር ሊጉ ጅማሬ በኤቨርተን መልካም አቋም ማሳየቱን ተከትሎ ሳውዝጌት ወደ ቡድኑ እንዲመለስ ፍላጎቱ መሆኑን በስልክ አሳውቆት ነበር።

አሰልጣኙ አናብስቱ ከማልታና ስሎቫኪያ ጋር ላለባቸው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እንዲጫዎት ጥሪ እንዳደረገለትም ተናግሯል።

ሩኒ ውሳኔውን አስመልክቶ ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ ጥሪውን ከአሰልጣኙ በመስማቱ መደሰቱን ገልጿል።

ይሁን እንጅ ከዚህ በኋላ ይህን ማድረጉ ከባድ በመሆኑ ለብሄራዊ ቡድኑ መጫወት እንደማይፈልግ ለአሰልጣኙ መግለጹንም ተናግሯል።

እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከቤተሰቡና ከክለብ አሰልጣኙ ጋር መወያየቱን የጠቀሰው ሩኒ፥ ከብሄራዊ ቡድኑ መነጠል እጅግ ከባድ ውሳኔ መሆኑንም ያነሳል።

ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን መጫወት ትልቅ ክብር ነው የሚለው ሩኒ በቡድኑ ውስጥ ለተባበሩኝ ምስጋናዬ ይድረሳቸውም ብሏል።

ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ስኬታማ አለመሆኑ እንደሚቆጨውም ነው የተናገረው።

አሁን ላይ አሰልጣኙ በያዘው ስብስብ ቡድኑን ወደ ስኬት እንደሚመራው እምነቱ መሆኑንም ገልጿል።

በቀጣይም ሙሉ ትኩረቱን በክለቡ ላይ ማድረግን ብቻ እንደሚመርጥም አስረድቷል።

ዋይኑ ሩኒ በ14 አመት የብሄራዊ ቡድን ቆይታው በ119 ጨዋታዎች 53 ጎሎችን በማስቆጠር ባለ ክብረወሰን ነው።