ሞሮኮ የ2026 የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት እንደመትወዳደር አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሀገሪቱ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2026 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት እንድምትወዳደር አስታውቋል።

የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት መወዳደር የሚፈልጉ ሀገራት ፍላጎታቸውን ለፊፋ የሚያሳውቁበት ቀነ ገደብ ዛሬ በሚጠናቀቅበት ጊዜ ነው ሞሮኮ ፍላጎቷን ያስታወቀችው።

አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲከኮ ባሳለፍነው ሚያዝያ ወር ላይ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2026 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ለመሆን እንደሚወዳደሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሞሮኮ የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ከአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ የምትወዳደር 4ኛዋ ሀገር ሆናለች።

ሞሮኮ ዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ስትወዳደር ይህ ለ5ኛ ጊዜ መሆኑም ታውቋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ሞሮኮ በ2026 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ እንድታዘጋጅ ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ሙሉ ድጋፍ መስጠቱን አይዘነጋም።

ፊፋ የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ማን ያዘጋጃል የሚለው ውሳኔም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2020 እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።

ዓለም ዋንጫ እስካሁን በአፍሪካ አህጉር አንድ ጊዜ ብቻ የተካሄደ ሲሆን፥ ይህም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት የተካሄደው ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2026 የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ላይ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር እንደሚጨምር መወሰኑ ይታወሳል።

ይህም አሁን በዓለም ዋንጫ ላይ የሚወዳደሩ ሀገራት ቁጥር ከ32 ወደ 48 እንዲያድጉ የሚያደርግ ነው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ