በፊፋ ወርሃዊ ደረጃ ኢትዮጵያ 16 ደረጃዎችን አሻሻለች

አዲስ አበባ ነሃሴ 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ወርሃዊው የሃገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 16 ደረጃዎችን ማሻሻል ችላለች።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ2018 የቻን ውድድር ለማለፍ በሀምሌ ወር ከጀቡቲ አቻው ጋር ያደረገውን የማጣሪያ ጨዋታ 5 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ዋልያዎቹ በአቋም መለኪያ ጨዋታ በሉሳካ ከዛምቢያ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ማጠናቀቃቸው አይነዘጋም።

ፊፋ ባወጣው የወሩ ደረጃ ብራዚል አንድ ደረጃ በማሻሻል አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ጀርመን ከመሪነቷ አንድ ደረጃ በመቀነስ ሁለተኛ ላይ ስትቀመጥ፥ አርጀንቲና በሀምሌ ወር ባለችበት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ በሰኔ ወር ከነበረችበት 136ኛ ደረጃ በሀምሌ ወር ወደ 120ኛ ደረጃ ከፍ ብላለች።

ከአፍሪካ ሀገራት ደግሞ 36ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ከአፍሪካ ግብፅ ቀዳሚ ስትሆን ከአለም 25ኛ ደረጃን ይዛለች፤ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ደግሞ ከአለም 28ኛ ከአፍሪካ ደግሞ ግብጽን ተከትላ 2ኛ ሆናለች።

ሴኔጋል ደግሞ 4 ደረጃዎችን በመቀነስ ከአለም 31ኛ ከአፍሪካ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በወሩ ናሚቢያ 20፣ ጃማይካ 19 እንዲሁም ላይቤሪያ 17 ደረጃዎችን በማሻሻል የተሻለ ወርሃዊ ደረጃ አግኝተዋል።

በአንጻሩ ኩራካዋ እና ኩባ 18 ደረጃዎችን በማሽቆልቆል የከፋ ውጤት አስመዝግበዋል።

አንጉሊያ፣ ባህማስ፣ ኤርትራ፣ ጅብራልተር፣ ሶማሊያ እና ቶንጋ ደግሞ አሁንም ያለምንም ነጥብ በደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።

fifa_ranking.png

 

 

 

ምንጭ፦ www.fifa.com