በሻምፒዮናው የሴቶች 5 ሺህ ሜትርን ጨምሮ 3 የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በለንደን አስተናጋጅነት ሰባተኛ ቀኑን በያዘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ምሽት በሚደረጉ ሶስት የማጣሪያ መርሃ ግብሮች ኢትዮጵያውያን ይሳተፋሉ፡፡

በመርሃ ግብሩ መሰረት ምሽት 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በሚካሄደው የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ለፍጻሜ ለመድረስ አልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪ እና ለተሰንበት ግደይ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ፡፡

ምሽት 3 ሰዓት ከ25 ላይ በሴቶች የ800 ሜትር ማጣሪያ ሃብታም አያሌው፣ ኮሬ ቶላ እና ማህሌት ሙሉጌታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለመግባት ይወዳደራሉ፡፡

የወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር ማጣሪያ ምሽት 4 ሰዓት ከ25 የሚካሄድ ሲሆን፥ አማን ወጤ፣ ሳሙኤል ተፈራ እና ተሬሳ ቶሎሳ ኢትዮጵያን ወክለው ወደ ግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ፡፡

ትናንት ምሽት ከ3 ሰዓት በኋላ በተካሄደው የሴቶች 3 ሺህ መሰናክል የማጣሪያ ውድድር ሶፊያ አሰፋ፣ እቴነሽ ዲሮ እና ብርቱካን ፈንቴ ተወዳድረዋል።

በማጣሪያ ውድድሩም እቴነሽ ዲሮ እና ብርቱካን ፈንቴ ጥሩ ሰዓት በማስመዝገባቸው ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል፡፡

ምሽት 4 ሰዓት ከ05 ላይ ደግሞ የወንዶች 5 ሺህ ሜትር ማጣሪያ ተካሂዶ ሶስት ኢትዮጵያውያን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈዋል።

በመጀመሪያው የማጣሪያ ምድብ ሙክታር እድሪስ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ የሮጡ ሲሆን ዮሚፍ 1ኛ እና ሙክታር 3ኛ በመውጣት ወደ ፍጻሜ ግብተዋል።

በሁለተኛው ምድብ የሮጠው ሰለሞን ባረጋ ከምድቡ 1ኛ በመውጣት ፍጻሜውን በብቃት ተቀላቅሏል።

በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ በአንድ የወርቅና በሁለት የብር ሜዳልያዎች ከዓለም አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ከአፍሪካ ደግሞ ከኬንያና ደቡብ አፍሪካ ቀጥላ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።