ሮናልዶን ወደ ዩናይትድ ማዛወር የማይቻል ነው - ሞሪንሆ

 

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ ክርስቲያኖ ሮናልዶን ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ማዛወር የማይቻል ነው ብለዋል።

አሰልጣኙ ይህን ያሉት ከወራት በፊት የእግር ኳስ ጥበበኛው ከሪያል ማድሪድ እለቃለሁ ማለቱን ተከትሎ ነው።

ተጫዋቹ ከስፔን ሊወጣ ይችላል የሚሉ ሪፖርቶች ሲወጡ የቆዩ ሲሆን አሁን ላይ ግን ጉዳዩ የተቀዛቀዘ መስሏል።

ሮናልዶም ውሳኔውን እንደሚያጤነው መናገሩ ይታወሳል።

ይሁንና የፖርቹጋላዊው ማረፊያ የቀድሞ ክለቡ ማንቸስተር ዩናየትድ ሊሆን ይችላል መባሉን ተከትሎ የቀያይ ሰይጣኖቹ አሰልጣኝ ሞሪንሆ ይህ ዝውውር ሊሳካ የማይችል መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ ዜና የቀድሞው የአርሰናል ተጫዋች እንግሊዛዊው ፖል ሜርሰን አርሰናል አሌክሲ ሳንቼዝን በክለቡ ማቆየት ካልቻለ ሰርጂዮ ኩን አጉየሮን ከማንቸስተር ሲቲ ማዛወር አለበት ብሏል።

የ49 ዓመቱ እንግሊዛዊ ይህን ያለው ሳንቼዝ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ በሚሳተፍ ክለብ መጫወት እፈልጋለሁ የሚል አስተያየት መሰንዘሩን ተከትሎ ነው።

የቀድሞው መድፈኛ ሜርሰን “አጉየሮ ከሳንቼዝ ይበልጣል፣ ስለዚህ ሳንቼዝ መልቀቅ እፈልጋለሁ ካለ እንዲለቅ መፍቀድና የሲቲውን አጥቂ ማስፈረም የተሻለ ነው” ብሏል።

ሜርሰን “እኔ በአርሰናል ክለብ ውስጥ የመወሰን ሰልጣን ቢኖረኝ የማደርገው ይህንኑ ነው” ብሏል።

አሌክሲስ ሳንቼዝ በአርሰናል አዲስ ኮንትራት ይፈርማል ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን አልፈረመም።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ተጫዋቹ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ሊያመራ ይችላል እየተባለ ሲሆን ከጀርመን ባየር ሙኒክ ከፈረንሳይ ደግሞ ፓሪሴንት ጄርሚን ፍላጎት እንዳላቸው ተዘግቧል።

በሌላ ዜና ኤሲ ሚላን የባየርሙኒኩን አማካይ ሬናቶ ሳንቼዝን ለማስፈርም ፍላጎት አለው ተባለ።

የባቫሪያኑ ክለብ ሊቀመንበር ካርል ሄንዝ ሩሚኒ ሚላን ተጫዋቹን ማስፈረም እንደሚፈልግ ይፋ አድርገዋል።

ኤሲሚላን በቀጣዩ የውድድር ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ ከፍተኛ ዝውውሮችን እየፈጸመ ነው።

በክረምቱ የዝውውር መስኮትም ሌኦናርዶ ቦኑቺን፣ ሪካርድ ሮድሪጌዝንና ሉካስ ቢግሊያን አስፈርሟል።

 

 

ምንጭ፦ ጎል ዶት ኮም