ፈረሰኞቹ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአገር ውሰጥ አራት ተጫዋቾችን አስፈርሟል።

ፈረሰኞቹ ጋዲሳ መብራቴን ከሃዋሳ ከተማ፣ አብዱልከሪም መሃመድን ከኢትዮጵያ ቡና፣ የሲዳማ ቡናውን ግብ ጠባቂ ለአለም ብርሃኑና አማካኙን ሙሉአለም መስፍንን ነው ያስፈረሙት።

አራቱም ተጫዋቾች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የጂቡቲ ጨዋታ መልስ ለአዲሱ ቡድናቸው ፊርማቸውን ማኖራቸውን ክለቡ አስታውቋል።

ሁሉም ተጫዋቾች ለሁለት ዓመት በክለቡ ለመጫወት የተስማሙ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ ለመጫወት በመፈረማቸው ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል ብሏል ክለቡ።

ተጫዋቾቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ከዘንድሮው ዓመት የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ያግዙታል ተብሏል።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት አራቱም ተጫዋቾች በነበሩበት ክለብ ጥሩ እንቅስቃሴ እንደነበራቸው ተገልጿል።

ክለቡ በቀጣይ የሚያስፈርማቸውን ተጫዋቾች በቅርቡ እንደሚያሳውቅም ነው ያስታወቀው።