አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በወላይታ ድቻ ውሉን አደሰ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሻምፒዮኑ ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በክለቡ ለመቆየት ውሉን አደሰ።

አሰልጣኙ ውሉን ያደሰው ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት መሆኑ ተገልጿል።

አሰልጣኝ መሳይ ውሉን ያደሰው ክለቡ በቀጣዩ የውድድር ዓመት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ መሳተፍ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ባሸነፈ ማግስት ነው።

አሰልጣኙ ከወላይታ ድቻ ጋር የተስማማበትን የክፍያ መጠን ክለቡ ከመግለጽ ቢቆጠብም ከዚህ ቀደም ከሚያገኘው የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በቀጣይ ክለቡን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል።

ለዚህም ከዚህ ቀደም ከነበረው የተጫዋች ግዢ ፖሊሲውን በተወሰነ መልኩ ሊለውጥ መሆኑም ተነግሯል።

ወላይታ ድቻ በ2001 ዓመተ ምህረት ሲመሰረት አሰልጣኝ ሆኖ የተሾመው የቀድሞው የአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ እና ኢትዮጵያ ቡና ኮከብ መሳይ ተፈሪ ላለፉት 8 አመታት በወላይታ ድቻ ቆይቷል።

 

 

 


ምንጭ፦ ሶከር ኢትዮጵያ