ሰርቢያዊው ድራጋን ፖፓዲች ኢትዮጵያ ቡናን በድጋሚ ሊያሰለጥኑ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሰርቢያዊውን አሰልጣኝ ድራጋን ፖፓዲች አሰልጣኝ አድርጎ ሊቀጥር መሆኑን አስታውቋል።

ድራጋን ፖፓዲች ቡድኑን ለመርከብ ዛሬ አዲስ አበባ እንደሚገቡም ነው ክለቡ በፌስቡክ ገፁ ላይ ያሰፈረው።

ኢትዮጵያ ቡና የቀድሞው የክለቡን ተጫዋች ካሳዬ አራጌ አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም ተቃርቧል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ሰንበተዋል።

ይሁን እንጂ ክለቡ በ2008 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቡድኑን ያሰለጠኑት ድራጋን ፖፓዲች የመጨረሻ ምርጫ አድርጓል።

ኢትዮጵያ ቡና ሰርቢያዊውን ነቦይሻ ቪችቼቪች ባለፈው ጥር ወር ማሰናበቱን ተከትሎ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ግርማን ዋና አሰልጣኝ፤ እድሉ ደረጀን ደግሞ ረዳት አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።

ቡድኑ በአሰልጣኝ ገዛኸኝ ግርማ እየተመራ ያስመዘገበው ውጤት አመርቂ አይደለም ያለው ክለቡ በቅርቡ የቀድሞ የቡድኑን ተጫዋች አቶ እድሉ ደረጀ በጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት፤ አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ደግሞ በጊዜያዊ ምክትል አሰልጣኝነት ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ መሾሙም አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት በፕሪሚየር ሊጉ በ47 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።