ቅዱስ ጊዮርጊስ የ2009 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮንነቱን አረጋገጠ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) 28ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ተካሂደዋል።

የሊጉ ባለ ክብረወሰን ቅዱስ ጊዮርጊስም የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል።

ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክን ያስተናገዱት ፈረሰኞች፥ በአዳነ ግርማ ጎል 1 ለ 0 አሸንፈዋል።

የዛሬውን ውጤት ተከትሎም ሊጉን ለ14ኛ ጊዜ አሸናፊ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ፈረሰኞቹ የዛሬውን ጨዋታ በማሸነፋቸው ነጥባቸውን 55 ሲያደርሱ፥ ተከታዮቹ ደደቢት እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ጥለዋል።

ደደቢት ዛሬ በመሸነፉ ባለበት 48 ነጥብ ላይ ሲቆም፥ ሲዳማ ቡና አቻ በመለያየቱ ነጥቡን ከደደቢት እኩል 48 አድርሷል።

ተከታዮቹ የቀራቸው ሁለት ጨዋታ ብቻ ሲሆን፥ ጊዮርጊስ ነጥቡን 55 በማድረሱ ቀሪ ጨዋታዎቹን ቢሸነፍም በአንድ ነጥብ ልዩነት ሻምፒዮንነቱን ያስከብራል።

ክልል ላይ በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች፥ በሶዶ ስታዲየም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው ወላይታ ዲቻ፥ በሜዳው የ 1 ለ 0 ሽንፈትን አስተናግዷል።

ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ ሰዓት ጎሏን አስቆጥራል።

በፋሲለደስ ስታዲየም መከላከያን ያስተናገደው ፋሲል ከነማም ጨዋታውን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

ወልዲያ ላይ ጅማ አባቡናን ያስተናገደው ወልዲያ ከተማ ጨዋታውን ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት አጠናቋል።

በተመሳሳይ ይርጋለም ላይ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና አርባ ምንጭ ከተማ ጨዋታም ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ጨዋታ ሆኗል።

ወደ አዳማ ያቀናው ደደቢት ደግሞ በአዳማ 2 ለ 1 ተሸንፏል፤ ዳዋ ሁቴሳ እና ታፈሰ ተስፋዬ ለአዳማ የድል ጎሎቹን ሲያስቆጥሩ።

የቀድሞውን የኢትዮ ኤሌክትሪክ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይን የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብረ ወሰን ለመስበር የተቃረበው ጌታነህ ከበደ ለደደቢት የማስተዛዘኛ ጎሏን አስቆጥሯል።

ወደ ድሬዳዋ ያቀናው ሃዋሳ ከተማ በድሬዳዋ ከተማ 1 ለ 0 ተሸንፏል።

አሸናፊው የተረጋገጠበት የዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ አዲስ የመጣው አዲስ አበባ ከተማን ወደ ታችኛው ሊግ ሸኝቶታል።

ቀሪ ሁለት ክለቦችም በቀጣይ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይታወቃሉ።

ኢትዮጵያ ንግድ ባነክ በ28 ነጥቦች ይዞ በቀሪዎቹ 180 ደቂቃዎች በሊጉ የመሰንበት እድሉን ይወስናል።

በአንጻሩ ጅማ አባ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ 29 ነጥብ በጎል ክፍያ 14ኛ እና 13ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ወላይታ ዲቻም በ30 ነጥቦች ላለመውረድ ሁለት 90 ደቂቃዎችን የሚጠብቅ ክለብ ሆኗል።

የምስራቁ ተወካይ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ፥ 31 ነጥቦች በመያዝ ሁለቱን ወራጅ ክለብ ኮታዎች ለመሙላት የሚደረገውን ትንቅቅንቅ ይጠባበቃል።

መከላከያ፣ ሃዋሳ እና ወልዲያ ከተማም በቅደም ተከተል 35 እና 34 ነጥቦች በመያዝ፥ በሊጉ ለመቆየት የአንድ ጨዋታ ውጤት ያስፈልጋቸዋል።

33 ነጥብ የያዘው አርባ ምንጭ ከተማም በ2010 በሊጉ ለመታየት አንድ ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

አሁን በያዙት ነጥብ የሚቆዩ ከሆነና ከታች ያሉት የመጨረሻዎቹ ሁለት ክለቦች ማሸነፍ ከቻሉ በሊጉ የመቆየት እድላቸው በጎል ክፍያ የሚወሰን ይሆናል።