ቼልሲ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሆነ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 5 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ቼልሲ ትናንት ምሽት ዌስትብሮምን ባሸነፈበት ጨዋታ የ2016/17 አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ሰማያዊዎቹ ትናንት ሚኪ ባትሹዋይ በ82ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ዌስት ብሮምን 1 ለ 0 በማሸነፍ ሁለት ጨዋታ እየቀራቸው የ2016/2017 የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

antonio_conte_victory.jpg

የአንቶኒዮ ኮንቴ ተጫዋቾች የሊጉ ሻምፒዮና መሆናቸውን ለማረጋጋጥ ትናንት ከዌስት ብሮም ተጫዋቾች ጋር የነበራቸው ፍልሚያ ከባድ ነበር፡፡

በ87 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ የተቀመጠው የዘንድሮው ሻምፒዮና ቼልሲ፥ ከኋላው ቶተንሃም ሆትስፐር በ77 ነጥብ፣ ሊቨርፑል በ70፣ ማንቼስተር ሲቲ በ69 ነጥብ ይከተሉታል፡፡

ቼልሲ በቀጣይ ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች የሚቀሩት ሲሆን፥ በ37ኛው ሳምንት ዋትፎርድን ሲገጥም፥ በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ግጥሚያ ደግሞ ሰንደርላንድን በስታምፎርድ ብሪጅ ያስተናግዳል፡፡

ሰማያዊዎቹ ከሰንደርላንድ ጋር በሚኖራቸው የሊጉ ጨዋታት ዕለት የድል ዋንጫቸውን የሚያነሱ ይሆናል፡፡

ቼልሲን ዘንድሮ የተረከቡት ጣሊያናዊው አሰልጣኝ አንቶኒዮ ኮንቴ የኤፍ ኤ ካፕ አሸናፊ ለመሆን ከአርሰናል ጋር በፈረንጆች ግንቦት 27 በፍጻሜ ይገናኛሉ፡፡

በትናንት ምሽት ሌላ ጫዋታ ኤቨርተን ዋትፎርድን አስተናግዶ 1 ለ 0 አሸንፏል፡፡

ዛሬ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 36ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲካሄዱ ማንቼስተር ሲቲ ሌሲስተርን ከቀኑ 8 ሰዓት ከ30 ይገጥማል፤ ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ ደግሞ ከሜዳው ውጭ አርሰናል ከስቶክ ሲቲ ጋር ይፋለማል፡፡