በእሁዱ የለንደን ማራቶን ቀነኒሳ እና ጥሩነሽ ይሳተፋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 13 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው ለንደን ማራቶን በመጪው እሁድ ይካሄዳል።

በዘንድሮው ውድድር ላይ ታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ከባድ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በወንዶች የሶስት ጊዜ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊው ቀነኒሳ በቀለ በውድድሩ የሚሳተፍ ሲሆን፥ የአሸናፊነቱን ቅድሚያ ግምትም አግኝቷል።

ቀነኒሳ በተለይም በበርሊን ማራቶን ያስመዘገበው ሰዓት፥ በእሁዱ የለንደን ጎዳና ከሚወዳደሩት መካከል ፈጣኑ ያደርገዋል።

ከቀነኒሳ በቀለ በተጨማሪ ፈይሳ ሌሊሳና ተስፋዬ አበራ በውድድሩ የሚጠበቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።

የቤጂንግ የአለም ሻምፒዮናን በ19 አመቱ ያሸነፈው ኤርትራዊ አትሌት ግርማይ ገብረስላሴም ብርቱ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሏል።

በጎረቤት ኬንያ በኩል አቤል ኪሩይና ዳንኤል ዋንጂሩ ይጠበቃሉ።

በሴቶቹ ምድብ ደግሞ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በውድድሩ ትካፈላለች።

ጥሩነሽ በመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯ ያስመዘገበችው የ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ35 ሰከንድ፥ በእሁዱ ውድድር እንድትጠበቅ አድርጓታል።

የለንደን ማራቶንን ሁለት ጊዜ ያሸነፈችው ኬንያዊቷ ሜሪ ኪታኒ ሌላዋ የአሸናፊነቱን ግምት ያገኘች አትሌት ሆናለች።

 

 

 

በእዩኤል ዘሪሁን