በፕሪሚየር ሊጉ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና አሸንፈዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ24ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን ኢትዮጵያ ቡና ወልድያን አሸንፈዋል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ላይ በተካሄደው ጨዋታ 5 ለ 3 በሆነ ውጤት ነው ያሸነፈው።

ፈረሰኞቹ የመጀመሪያውን ግማሽ ጨዋታ በመሀሪ መና፣ አዳነ ግርማ እና ሳልሃዲን ሰዒድ ግቦች 3 ለ 0 እየመሩ ለዕረፍት ወጥተው ነበር፡፡

ከዕረፍት መልስ ሳልሃዲን እና ፕሪንስ ሰቨርኒኾ ባስቆጠሯው ተጨማሪ ሁለት ግቦች እስከ 82ኛው ደቂቃ ጊዮርጊስ 5 ለ 0 ሲመራ ነበር፡፡

ድሬዳዋ ከተማ በ85ኛ ደቂቃ በበረከት ይስሐቅ እንዲሁም 87 እና 92ኛው ደቂቃ ላይ ይሁን እንደሻው ሶስት ግቦችን ቢያስቆጥሩም ከመሸነፍ አልዳነም፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ወልድያ ከተማን በአዲስ አበበ ስታዲያም አስተናግዶ 2 ለ 1 ረቷል፡፡

ቡና በጋቶች ፓኖም እና በሳሙኤል ሳኑሚ ሁለት ግቦች መደበኛውን ጨዋታ 2 ለ 0 ሲመራ ቆይቷል፡፡

የመሃል አልቢትሩ በጨመሩት ደቂቃም ወልድያ ከተማ ሙሉጌታ ረጋሳ በ93ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ባሳረፋት ግብ ከባዶ ከመሸነፍ ድኗል፡፡

ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ43 ነጥብ ሲመራ ሲዳማ ቡና በ42 ደደቢት በ41 ነጥቦች ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነው ይከተላሉ፡፡

ጅማ አባቡና፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማ በሊጉ ግርጌ ይገኛሉ፡፡