ጁቬንቱስ እና ሞናኮ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 12 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻምፒየንስ ሊጉ የሩብ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት ተደርገዋል።

በካምፕ ኑ ጁቬንቱስን ያስተናገደው ባርሴሎና የመጀመሪያውን ውጤት መቀልበስ አልቻለም።

በስታድ ሉዩዝ 2ኛ ደግሞ ሞናኮ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ በቻምፒየንስ ሊጉ ሶስት ጎሎች ያስቆጠረበትን ምሽት አሳልፏል።

ሲጠበቅ በነበረው የካምፕ ኑ ጨዋታ ባርሴሎናዎች በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢጫወቱም የቱሪኑን ሽንፈት መቀልበስ አልቻሉም።

ባርሴሎናዎች በሊዮኔል ሜሲ በሰርጅ ሮቤርቶ መልካም የሚባሉ አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ወደ ጎልነት መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።

አዲስ ነገር ቢጠበቅም ጨዋታው ያለምንም ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጁቬንቱስም የመጀመሪያ የ3 ለ 0 ድላቸውን በጠንካራ የቡድን ስራ አስጠብቀው ወጥተዋል።

በስታድ ሉዊዝ 2ኛ ቦሩሲያ ዶርትመንድን ያስተናገደው ሞናኮ 3 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

ወጣቱ አጥቂ ምባፔ፣ ራዳሜል ፋልካኦ እና ገርሜይን ቡድናቸውን ባለ ድል ያደረጉ ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ለዶርትመንድ ማርኮ ሪውስ የማስተዛዘኛዋን ጎል አስቆጥሯል።

ሞናኮም በድምር ውጤት 6 ለ 3 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል ችሏል።

ከትናንት በስቲያ በተደረጉ ጨዋታዎች ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀላቸው ይታወሳል።

ዛሬ በዩሮፓ ሊግ አራት ጨዋታዎች ተደርገው ግማሽ ፍጻሜውን የሚቀላቀሉ ቡድኖች ይለያሉ።