ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ወደ ምድብ ድልድል መግባቱን አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቅዱስ ጊዮርጊስ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባቱን አረጋገጠ።

ከኮንጎው ኤሲ ሊዮፓርድስ ጋር የመልስ ጨዋታውን ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 2 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

በዚህም በድምር ውጤት 3 ለ 0 በመርታት በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጨረሻ 16 ቡድኖች ውስጥ መቀላቀሉን አረጋግጧል።

የማሸነፊያ ግቦቹንም ሳላዲን ሰይድ በ16ኛው እና በ91ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ምድብ ድልድሉ መግባቱን ተከትሎ 550 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚያገኝ ይሆናል።

በ2017ቱ የቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ የሲሸልሱን ኮቲዲኦር በደርሶ መልስ በመርታት ወደ ጥሎ ማለፉ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ፥ ኤሲ ሊዮፓርድስን ባሳለፍነው ሳምንት በዶሊሴ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

 

 

 

 

በፋሲካው ታደሰ