በቻምፒየንስ ሊጉ ሩብ ፍጻሜ ሙኒክ ከማድሪድ ባርሴሎና ከጁቬንቱስ ይጫወታሉ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ድልድል ዛሬ ይፋ ሆኗል።

የቻምፒየንስ ሊጉ እንግዳ ቡድን ሌሲስተር ሲቲ ከዲያጎ ሲሞኒው አትሌቲኮ ማድሪድ ጋር ደርሶታል።

ሁለቱ ቡድኖች የዛሬ 20 አመት በአውሮፓ ማህበረሰብ (አሁን ዩሮፓ ሊግ) ዋንጫ ተገናኝተው አትሌቲኮ ማድሪድ በደርሶ መልስ 4 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ለዚህ መድረክ ያበቋቸውን አሰልጣኝ ክላውዲዮ ራይኔሪን ያሰናበቱት ቀበሮወቹ

የ20 አመት በቀላቸውን ለመቀልበስ እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ደግሞ ከፈረንሳዩ ሞናኮ የሚገናኙ ይሆናል።

በአውሮፓ ከየትኛውም ክለብ በላይ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠሩት ሞናኮዎች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጭ በሲግናል ኤዱና ፓርክ ያደርጋሉ።

የውድድሩ ባለ ክብረ ወሰን ሪያል ማድሪድ ወደ ጀርመን አቅንቶ በቀድሞ አሰልጣኙ የሚመራውን ባየርን ሙኒከን ይገጥማል።

ካርሊቶም በግዙፉ የአውሮፓ እግር ኳስ መድረክ እየመሩ ለድል ያበቁትን ክለብ በተቃራኒነት ይገጥማሉ።

ባየርን ሙኒክ በአውሮፓ መድረክ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች በማድሪድ ላይ የበላይነት አለው።

ከቡድኖቹ ወቅታዊ አቋም አንጻርም ጨዋታው ተጠባቂ ይሆናል።

ባርሴሎና ደግሞ የጣሊያኑን ጁቬንቱስ ያስተናግዳል።

ሁለቱ ክለቦች በተገናኙባቸው የአውሮፓ መድረክ ጨዋታዎች እኩል ጊዜ ተሸናንፈዋል።

በ2015ቱ ፍጻሜ ደግሞ ባርሴሎና 3 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።

የመጀመሪያ ጨዋታዎች ሚያዚያ 3 እና 4 ተካሂደው የመልስ ጨዋታዎች ደግሞ በሳምንቱ ይደረጋሉ።

አሸናፊዎቹም ለካርዲፉ የፍጻሜ ጉዞ የሚረዳውን የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ያደርጋሉ።

በሌላ በኩል የዩሮፓ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ድልድልም ይፋ ሆኗል።

በፕሮግራም አወጣጥ ተበድለናል በማለት የሚያማርሩት ጆዜ ሞሪንሆ ማንቼስተርን ይዘው የቤልጅየሙን አንደርሌክት ይገጥማሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ መድረክ ሁለት ጊዜ (በደርሶ መልስ አራት ጨዋታ አድርገዋል) ተገናኝተዋል።

በቀድሞ መጠሪያው ዩሮፒያን ካፕ በሚባለው የአሁኑ ቻምፒየንስ ሊግ በ19 56/57 ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታቸው ማንቼስተር በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፏል።

በወቅቱ በሰር ማት በዝቢ የሚመራው ማንቼስተር ከሜዳው ውጭ 2 ለ 0 አሸንፏል።

በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ በኦልድትራፎርድ አንዳንድ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ስለነበር፥ በማንቼስተር ሲቲ ሜይን ሮድ ስታዲየም አድርጎ 10 ለ 0 በማሸነፍ በአውሮፓ መድረክ በሰፊ የጎል ልዩነት ያሸነፈበትን ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።

ከዚያ በኋላም በፈረንጆቹ 2000/01 በቻምፒየንስ ሊጉ ተገናኝተው ኦልድትራፎርድ ላይ ማንቼስተር 5 ለ 1 ሲያሸንፍ፥ በቫንደን ስቶክ ላይ ደግሞ አንደርሌክት 2 ለ 1 አሸንፏል።

ተመጣጣኝ በሚመስለው ድልድል የስፔኑ ሴልታ ቪጎ ከቤልጅየሙ ክለብ ጌንክ ጋር ይጫወታል።

የቀድሞው ሃያል ክለብ አያክስ አምስተርዳም ደግሞ ከጀርመኑ ሻልከ 04 ይፋለማል።

ጠንካራው ሊዮን አስቸጋሪውን ጨዋታ ከቤሺክታሽ ጋር ያከናውናል።

የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ሚያዚያ 5 ተካሂደው በሳምንቱ የመልስ ጨዋታወች ከተደረጉ በኋላ የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች ይለያሉ።