ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሊዮፓርድስ ጋር እሁድ የመልስ ጨዋታውን ያደርጋል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የመልስ ጨዋታውን እሁድ 10 ስአት ላይ ያደርጋል።

በ2017ቱ የቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ የሲሸልሱን ኮቲዲኦር በደርሶ መልስ በመርታት ወደ ጥሎ ማለፉ የገባው ቅዱስ ጊዮርጊስ፥ የኮንጎውን ተወካይ ሊዮፓርድስ ባሳለፍነው ሳምንት በዶሊሴ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ፈረሰኞቹ ወደ ቀጣዩ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ምድብ ድልድል ለመግባት በአዲስ አበባ በሚደረገው ጨዋታ አቻ መውጣት በቂያቸው ነው።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በዶሊሴ ከተማ ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረው ምንተስኖት አዳነ በቀይ ካርድ በመውጣቱ ምክንያት በመልሱ ጨዋታ አይሰለፍም።

ከነገ በስቲያ የሚደረገው ጨዋታ በአቻ ውጤት አልያም በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናነት የሚጠናቀቅ ከሆነ ቅዱስ ጊዮርጊስ 550 ሺህ የአሜሪካ ዶላርየሚያገኝ ይሆናል።

 

በሀብታሙ ገደቤ