በዩሮፓ ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ሊዮን እና አያክስ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩሮፓ ሊግ ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ቡድኖች ትናንት ማምሻውን በተደረጉ ጨዋታዎች ተለተይዋል።

በኦልድትራፎርድ የሩሲያው ሮስቶቭን ያስተናገደው ማንቼስተር ዩናይትድ በሁዋን ማታ ብቸኛ ጎል 1 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

በመጀመሪያው ጨዋታ ሩሲያ ላይ 1 ለ 1 መለያየታቸውን ተከትሎም በደርሶ መልስ ማንቼስተር ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

በጥሎ ማለፉ ከባድ ጨዋታ የነበረው የሮማ እና የሊዮን ጨዋታ በስታዲዮ ኦሎምፒኮ ተካሂዷል።

ሮማ ጨዋታውን 2 ለ 1 ማሸነፍ ቢችልም በመጀመሪያው ጨዋታ 4 ለ 2 በመሸነፉ በድምር ውጤት ከሩብ ፍጻሜው ውጭ ሆኗል።

በአምስተርዳም አሬና ኮፐን ሃገንን ያስተናገደው አያክስ አምስተርዳም 2 ለ 0 አሸንፏል።

በደርሶ መልስ ውጤትም 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ችሏል።

ሻልከ እና ቦሩሲያ ሞንቼግላድባህ በቦሩሲያ ፓርክ ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ ተጠናቋል።

ሻልከ ከሜዳው ውጭ ብዙ ባገባ በሚለው ሩብ ፍጻሜው ተቀላቅሏል።

የቤልጅየሞቹ ጌንት እና ጌንክ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ሲጠናቀቅ ጌንት 6 ለ 3 በሆነ የድምር ውጤት አላፊ ሆኗል።

አንደርሌክት የቆጵሮሱን አፖል ኒኮሲያ አስተናግዶ 1 ለ 0 አሸንፏል፤ በደርሶ መልስ ውጤትም 2 ለ 0 በማሸነፍ የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋግጧል።

ወደ ሩሲያ ያቀናው ሴልታቪጎ ክራስኖዳርን 2 ለ 0 በማሸነፍ በድምር የ4 ለ 1 ውጤት በሩብ ፍጻሜው ስፔንን ይወክላል።

ቤሺክታሽ በሜዳው ኦሊምፒያኮስን 4 ለ 1 ሲያሸንፍ በደርሶ መልስ የ 5 ለ 2 ውጤት ሩብ ፍጻሜ መግባቱን አረጋግጧል።

ዛሬ ከሰዓት በኋላ በስዊዘርላንድ ኒዮን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ድልድል ይወጣል።