በዩሮፓ ሊግ ሮማ ከሜዳው ውጭ በሰፊ የጎል ልዩነት አሸንፏል

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የዩሮፓ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ትናንት ምሽት በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ተደርገዋል።

በምሽቱ ጨዋታዎች አብዛኛዎቹ ታላላቅ ቡድኖች ድል ቀንቷቸዋል።

የእንግሊዙ ማንቼስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድትራፎርድ የፈረንሳዩን ሴንት ኤቲየንን አስተናግዶ 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል።

የድል ጎሎቹን ስዊድናዊው አጥቂ ዝላታን ኢብራሂሞቪች በማስቆጠር በክለቡ የመጀመሪያ ሃትሪኩን ሰርቷል።

በጥሎ ማለፉ ከባድ ጨዋታ ኤል ማድሪጋል ላይ ቪያሪያል ከጣሊያኑ ሮማ ተጫውተዋል።

ቢጫ ሰርጓቾቹ የመጀመሪያ የጥሎ ማለፍ ጨዋታቸውን 4 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል።

የመልሱን ጨዋታ ሮማ በሜዳው እንደማድረጉ ቀጣዩን ዙር ከወዲሁ የተቀላቀለ ይመስላል።

ወደ ጀርመን ያቀናው ሌላው የጣሊያን ክለብ ፊዮረንቲናም በድል ተመልሷል።

ፊዮረንቲና ከሜዳው ውጭ ቦሩሲያ ሞንቼ ግላድባህን 1 ለ 0 አሸንፎ ተመልሷል።

ወደ ቤልጅየም ያመራው የእንግሊዙ ቶተንሃም ደግሞ በጌንት 1 ለ 0 ተሸንፏል።

የፈረንሳዩ ሊዮን ወደ ሆላንድ አምርቶ ኤ ዜ ድ አልክማርን 4 ለ 1 አሸንፎ ሲመለስ፥ በሳን ማሜስ አትሌቲክ ቢልባኦ አፖል ኒኮሲያን 3 ለ 2 አሸንፏል።

ሻልከ 04 ደግሞ ወደ ግሪክ አምርቶ ፓኦክን 3 ለ 0 ማሸነፍ ችሏል፤ ሴልታቪጎም ከሜዳው ውጭ ሻክታር ዶኔስክ 1 ለ 0 መርታት የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል።

የፖላንዱ ሊጋ ዋርሶው አያክስ አምስተርዳምን ያስተናገደበት ጨዋታ ደግሞ ያለምን ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

አንደርሌክት ዜኒት ሴንት ፒተርስበርግን 2 ለ0 ሲያሸንፍ፣ አስታራ ከጌንክ ሁለት አቻ ተለያይተዋል፤ ሉዶጎሬትስ ደግሞ በኮፐንሃገን 2 ለ 1 ተሸንፏል።

ኦሊምፒያኮስ ደግሞ በሜዳው ከኦስማን ሊስፓሮ ተጫውቶ፥ ያለምንም ጎል ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት አጠናቋል።

ሮስቶቭ ስፓርታ ፕራግን 4 ለ0፣ ክሪስኖዳር ፌነርባቼን 1 ለ 0 ሲያሸንፉ ቤሺክታሽ ከሜዳው ውጭ ሃፑየል ቤር ሸባን 3 ለ 1 አሸንፎ ተመልሷል።

የመልስ ጨዋታዎች በቀጣዩ ሳምንት ተካሂደው ሁለተኛውን የጥሎ ማለፍ ዙር የሚቀላቀሉ 16 ቡድኖች ይለያሉ።