ሙኒክ በአሊያንዝ አሬና አርሰናልን በሰፊ የግብ ልዩነት አሸንፏል

አዲሰ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትናንት ምሽት በተደረጉ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ባየር ሙኒክ እና ሪያል ማድሪድ ድል ቀንቷቸዋል።

አርሰናል በአሊያንዝ አሬና በባየር ሙኒክ 5 ለ 1 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሙኒክ በ11ኛው ደቂቃ በአርያን ሮበን ድንቅ ግብ፤ አርሰናል ደግሞ በአሌክሲስ ሳንቼዝ ጎል 1 ለ 1 አቻ ተለያይተዋል።

አራት ግቦችን በሁለተኛው አጋማሽ ያስተናገዱት መድፈኞቹ በቻምፒዮንስ ሊጉ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት የነበራቸው ተስፋ ተመናምኗል።

በቻምፒዮንስ ሊጉ 16 ጊዜ በጥሎ ማለፉ የተሰናበቱት መድፈኞቹ ሁለት ጊዜ በባየር ሙኒክ ተሸንፈው ከውደደሩ ውጭ ሆነዋል።

ይሁን እንጂ እሰካሁን አምስት ግብ አስተናግደውም ሆነ 25 በመቶ የኳስ ቁጥጥር ይዘው ተሸንፈው አያውቁም።

የአርሰን ቬንገር ቡድን ሎረንት ኮሸለኒ በሁለተኛው አጋማሽ በጉዳት ከተቀየረ በኋላ ሙኒክን መቋቋም ተስኖታል።

በ10 ደቂቃ ውስጥም ሮበርት ሎዋንዶውሰኪ እና ቲያጎ አልካንትራ ሶስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ስፔናዊው አማካይ ቲያጎ አልካንትራ በጨዋታው ሁለት ግቦችን ከማስቆጠሩ ባለፈ በ88ኛው ደቂቃ ቶማስ ሙለር ላስቆጠራት ግብ ሚናው ከፍተኛ ነበር።

መድፈኞቹ ሩብ ፍፃሜውን ለመቀላቀል በቀጣይ በኤሚሬትስ የሚያደርጉትን ጨዋታ በ5 የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

collage.jpg

በሌላ የቻምፒዮንስ ሊጉ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሪያል ማድሪድ በበርናባው ናፖሊን 3 ለ 1 ረቷል።

ናፖሊ በሎሬንዜ ኢንሲኔ ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ካሪም ቤንዜማ፣ ቶኒ ክሮስ እና ካዚሚሮ ሪያል ማድሪድን ለድል ያበቁ ግቦችን አስቆጥረዋል።

ናፖሊ መጋቢት 7 2017 በሜዳው ሪያል ማድሪድን ያስተናግዳል። አርሰናልም በተመሳሳይ ቀን በኤሚሬትስ ባየር ሙኒክን ይገጥማል።

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ