የአበበ ቢቂላ ስታዲየም በ105 ሚሊየን ብር ጥገናና ጣሪያ የማልበስ ስራ ሊከናወንለት ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የትራክ ንጣፍ እና ጣሪያ ማልበስ ስራን ለማከናወን ስምምነት ተፈረመ።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እና የቻይናው ዙዋንግንሚን ኩባንያ ናቸው ስምምነቱን የተፈራረሙት።

የስታዲየሙን የትራክ ንጣፍ እና ጣሪያ ማልበስ ስራ 105 ሚሊየን ብር ወጪ የሚደረግበት ይሆናል።

ስራው በ18 ወራት ውስጥ እነደሚጠናቀቅም ተጠቁሟል።

ስታዲየሙ ከዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ እድሳት እንደሚደረግለት ነው የቢሮው ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እና የኩባንያው ተወካይ ዋንግ ሁ ስምምነቱን ሲፈራረሙ የተገለፀው።

በጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ የተሰየመው ስታዲየሙ በተለያየ ጊዜ ጥገና እንዲደረግለት ጨረታ ቢወጣም በዲዛይን ጥራት ችግር በሚፈለገው ፍጥነት ሊታደስ አልቻለም።

የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮ የጥገና ስራው ጥራቱን ጠብቆ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ አደርጋለሁ ብሏል።

 

 

በኢዩኤል ዘሪሁን