ፌዴሬሽኑ የዕድሜ ተገቢነት ድንገተኛ ማጣራት ማድረግ ጀመረ

አዲሰ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዕድሜን ተገቢነት ችግር ለመፍታት ድንገተኛ ማጣራት ማድረግ መጀመሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለጸ።

ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ስፖርተኞችን የዕድሜ ተገቢነት ድንገተኛ የማጣራት ስራ ትናንት መጀመሩን ገልጿል።

የኤም.አር.አይ እና አካላዊ የዕድሜ ተገቢነት ምርመራው ከስፖርት ህክምና ቋሚ ኮሚቴና ከውድድር ዳይሬክቶሬት በተውጣጡ ሙያተኞች በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተጫዋቾች ላይ ነው በመካሄድ ላይ ያለው።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ተጨዋቾች በትክክለኛው የምርመራ ውጤት መሰረት ተሰልፈው ስለመጫወታቸው የሚያረጋግጥ ድንገተኛ ምርመራ ማድረጉንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

የምርመራ ስራው በሌሎች ክለቦች ላይ እንደሚቀጥልና ውጤቱም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን ገልጿል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ተግባራዊ በሆነው የኤም.አር.አይ እና አካላዊ የዕድሜ ተገቢነት ምርመራ ክለቦች ካቀረቧቸው 2 ሺህ 10 ተጫዋቾች መካከል 762ቱ ምርመራውን ማለፋቸው ይታወቃል።

ምንጭ፦ ኢዜአ