አሰልጣኙን ያሰናበተው ኢትዮጵያ ቡና ድል ቀንቶታል

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች በተደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ቀጥለው ውለዋል።

ዛሬ በ9 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ አርባምንጭን ያስተናገደ ሲሆን፥ ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ የበላይነት ተጠናቋል። 

ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን፥ ፀጋዬ አበራ በ36ኛው ደቂቃ እንዲሁም ገብረሚካኤል ያዕቆብ በ41ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች አርባምንጭን አሸናፊ አድርገዋል።

መከላከያን በባዶ ከመውጣት የታደገችውን ጎል ሳሙኤል ታዬ በ78ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል።

ክልል ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ከቀኑ በ9 ሰዓት ጎንደር ላይ ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ በፋሲል ከነማ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማን አሸናፊ ያደረገችውን ጎል ሄኖክ ገምቴሳ በ27ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል።

በተመሳሳይ ከቀኑ በ9 ሰዓት ወላይታ ዲቻ በሜዳው ሶዶ ስታዲየም ጅማ አባቡናን ያስተናገደ ሲሆን፥ ጨዋታውም በወላይታ ዲቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የወላይታ ዲቻን የማሸነፊያ ጎልም በዛብህ መለዮ በ28ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ይርጋለም ላይ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና የኢትዮ ኤሌክትሪክን ጨዋታ ደግሞ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በጨዋታው ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ፍጹም ገብረማርያም በ11ኛው ደቂቃ እንዲሁም አብይ በየነ በ85ኛው ደቂቃ ለሲዳማ ቡና የአቻነት ጎሎቹን ከመረብ አሳርፈዋል።

በሊጉ በጎል ልዩነት ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 2ለ1 በሆነ ውጤት ረቷል።

ለአዳማ ከተማ ሁለቱንም ጎሎች ቡልቻ ሹራ በ63ኛው እና በ88ኛው ደቂቃ ከመረብ ሲያሳርፍ፥ ለአዲስ አበባ ከተማ ደግሞ እንየው ካሳሁን በ75ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ከቀኑ በ10 ሰዓት ላይ ድሬዳዋ ላይ ድሬደዋ ከተማ ከደደቢት ተገናኝተው፥ ጨዋታው 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

እንዲሁም 11:30 ላይ ደግሞ አሰልጣኙን ያሰናበተው ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ጋር ጨዋታውን አድርጓል።

አሰልጣኙን ማሰናበቱን ይፋ ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና በጊዜያዊነት ክለቡን እንዲያሰለጥኑ በተሾሙት አዲስ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ሜዳ ገብቶ ድል ተቀዳጅቷል።

ጨዋታውንም በአስቻለው ግርማና ጋቶች ፓኖም ሁለት ጎሎች፥ 2 ለ 1 አሸንፏል፡፡

በሊጉ ቀሪ አንድ ጨዋታ በነገው እለት የሚካሄድ ሲሆን፥ በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዲያ ከነማን 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ያስተናግዳል።

በሙለታ መንገሻ

android_ads__.jpg