ኢትዮጵያ ቡና ሰርቢያዊውን አሰልጣኝ ነቦይሻ ቪችቼቪችን አሰናበተ

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ሰርቢያዊውን የክለቡን አሰልጣኝ ነቦይሻ ቪችቼቪች ማሰናበቱን አስታወቀ።

ዋና አሠልጣኝ ነቦይሻ ቪችቼቪች ከዛሬ ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ክለቡ በፌስቡክ ገጹ ላይ ይፋ አድርጓል።

አሰልጣኙ ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የተወሰነበትን ዝርዝር ሁኔታ በቀጣይ እንደሚያሳውቅም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ገልጿል።

ሰርቢያዊው ነቦይሻ ቪችቼቪች በዓመቱ መጀመሪያ ክለቡን የተቀላቀሉ ቢሆንም፥ በአሰልጣኝነት ቆይታቸው ለክለቡ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻሉም።

አሰልጣኙ በእስካሁን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቆይታቸውም ማሸነፍ የቻሉት ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ነው።

ቪችቼቪች በ9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከወልዲያ ከነማ ጋር በመልካቆሌ ላይ 1ለ0 የተሸነፉበት ጨዋታ የመጨረሻቸው ሆኗል።

ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ነቦይሻ ቪችቼቪች መሰናበታቸውን ተከልተሎም በዋና አሠልጣኝነት አሠልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ እንዲሁም በረዳት አሠልጣኝነት አሠልጣኝ እድሉ ደረጄ በጊዜያዊነት ክለቡን እንዲመሩ መሾማቸውንም ክለቡ አስታውቋል።

viche_2.jpgviche_3.jpg

አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ክለቡን በረዳት አሰልጣኝነት ሲመሩ የነበረ ሲሆን፥ አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ የኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድንን አሰልጣኝነት በመምራት ላይ ነበሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ ቡና በዛሬው እለት ከሃዋሳ ከተማ ጋር የሚያደርገውን የ10ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታም በአዳዲሶቹ አሰልጣኞች እየተመራ የሚያካሂድ መሆኑም ተነግሯል።

በሙለታ መንገሻ