ወልድያ ከተማ በመልካ ቆሌ ኢትዮጵያ ቡናን ረቷል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ወልድያ ከተማ በስታዲየሙ መልካ ቆሌ የመጨረሻ ጨዋታውን አድርጎ ድል ቀንቶታል።

በ9ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ መርሃ ግብር ወልድያ ኢትዮጵያ ቡናን አስተናግዶ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ብቸኛዋን የማሸነፊያ ግብ በድሩ ኑርሁሴን በ1ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።

ይህን ተከትሎም ወልዲያ ከኢትዮጵያ ቡና እኩል 10 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ በልጦ 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ዛሬ በመልካ ቆሌ የመጨረሻውን ጨዋታውን ያደረገው ወልድያ ከተማ በቀጣይ አዲስ በተገነባው መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም ጨዋታዎቹን የሚያደርግ ይሆናል። 

ትናንት በተደረጉ የሊጉ መርሃ ግብሮች የሊጉ መሪዎች ደደቢት እና አዳማ ከተማ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። 

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቀው።

ከሜዳው ውጭ አርባምንጭ ከተማን የገጠመው ደደቢት 1 ለ 1 አቻ ወጥቷል።

ሃዋሳ ከተማ ከወላይታ ዲቻ ያደረጉት ጨዋታም 3 ለ 3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ጅማ አባ ቡና ከሲዳማ ቡና ተጫውተው ባለ ሜዳው ጅማ አባ ቡና ጨዋታውን 2 ለ 0 አሸንፏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከድሬዳዋ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ በፈረሰኞቹ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተደምድሟል።

ፕሪሚየር ሊጉን ደደቢት እና አዳማ ከተማ በእኩል 18 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ይመራሉ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 ነጥብ ይከተላል።

አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ፋሲል ከተማ እና መከላከያ ደግሞ በእኩል 15 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀዋሳ ከተማ በ6 ነጥብ፣ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በ5 ነጥብ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።

ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ጌታነህ ከበደ በ9 ጎሎች ሲመራ፣ አዳነ ግርማ በ5፣ ሳላዲን ሰይድ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ኤዶም ሆርሶውኪ በእኩል አራት ግቦች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።

 

በሀብታሙ ገደቤ

 

android_ads__.jpg