12ቱ ታዳጊ ታይላንዳውያንን ወክሎ ይናገር የነበረው ማይናማራዊ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታይላንድ ማክሰኞ ዕለት ከዋሻ ሙሉ ለሙሉ መውጣታቸው የተነገረው ከ12ቱ የእግርኳስ ታዳጊ ተጫዋቾች መካከል አንደኛው የማይናማር ተወላጅ ነው፡፡

ይህ ታዳጊ አዱል ሳም-ኦን ይባላል ዕድሜው 14 መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

በሁለት ሳምንት የዋሻ ቆይታቸው ሁሉንም ታዳጊዎች በመወከል ውጪ ካለው ዓለም ጋር ይነጋገር የነበረው አዱል መሆኑ ይታወሳል፡፡

አዱል ከ11 ጓደኞቹ መካከል ከነፍስ አድን ባለሙያዎች ጋር በእንግሊዘኛ የሚግባባው ብቸኛው ታዳጊ ነበር በዚህም ለታይላንዳውያንና ለዓለም ድምጹን ያሰማው የመጀመሪያው ታዳጊ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ይህ ታዳጊ ታዲያ ገና በዚህ ዕድሜው አምስት ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል ተብሎዋል፡፡

አቀላጥፎ ከሚናገራቸው ቋንቋዎች መካከልም እንግሊዘኛ፣ ታይ፣ በርምኛ እና መንደሪን ይገኙበታል፡፡

አዱል ዓለም ዕውቅና ቢነፍጋትም ከማይናማር በመነጠል እራስ ገዝነት ባወጀችው በዋ ግዛት ውስጥ ነው የተወለደው፡፡

ታይላንዳዊ ታዳጊ ጓደኞችንም ሊቀላቀላቸው የበቃው የተሻለ ትምህርት ፍለጋ ወደ ሰሜናዊ ታይላንድ ለመማር በመምጣቱ ምክንያት ነው ተብሏል፡፡

አዱል ከእግኳስ ውጪ ፒያኖ ይጫወታል እንዲሁም ለትምህርት ቤቱ በርካታ ሜዳሊያዎችን ማምጣቱንም መምህራኖቹ መስክረዋል፡፡

በማይናማር ጦርና ግዛቷን ነጻ ለማውጣት በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል በሚደረግ ውጊያ ታዲያ ወደ ታይላንድ ተሰደው የሚኖሩ 400 ሺ ሀገር አልባ ዜጎች መኖራቸውን የተመድ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

 

ምንጭ፦ዴይሊይሜይል
በአብርሃም ፈቀደ