በ6 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የተሸጠው ባለ ሰማያዊ ቀለም አልማዝ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ300 ዓመታት በፊት በንጉሳውያን ቤተሰቦች ዘንድ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ባለ ሰማያዊ ቀለም አልማዝ ለጨረታ ቀርቦ ውድ በሆነ ዋጋ መሸጡ ተሰምቷል።

በጄኔቫ ለጨረታ የቀረበው አልማዙ ከተገመተው ዋጋ በላይ በ6 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር መሸጡም ተነግሯል።

ባለ ሰማያዊ ቀለም የአልማዝ ቀለበቱ የፓርማው ንጉስ ልጅ የሆነችው ልእልት ኤልሳቤጥ ፍራንሴ የስፔኑን ፍሊፕ አምስኛ ባገባችበት ወቅት በአውሮፓውፓውያኑ 1715 ነበር በስጦታ መልክ የተበረከተላት።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮም አልማዙ በተለያዩ ትውልዶች ቅብብሎሽ ከስፔን ወደ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን እና አውስትራሊያ ሲዘዋወር ቆይቷል።

ባለ 6 ነጥብ 1 ካራት አልማዙ ጎልኮንዳ ከተባለ ታዋቂው የህንድ የማእድን ማውጫ ስፍራ የተገኘ መሆኑም ተነግሯል።

ታዲያ ከሰሞኑ ለጨረታ የቀረበው አልማዙ፤ ለጨረታ በቀረበ በደቂቃዎች ቆይታ ውስጥ ነበር መሸጥ የቻለው።

አልማዙ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን እስከ 5 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያወጣል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፥ ከተገመተው በላይ በ6 ነጥብ 7 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ተሽጧል።

ባለ ሰማያዊ ቀለም የአልማዙን የገዛው ግለሰብ ማንነት ግን እስካሁን ይፋ አልተደረገም ተብሏል።

ምንጭ፦ www.bbc.com