በየዓመቱ ከፍታዋ በ2 ሳንቲ ሜትር የሚጨምረው ከተማ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በብሪታንያ ዴቮን የምትገኘው አነስተኛ ከተማ ከፍታዋ በየዓመቱ እየጨመረ መምጣቱን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩት።

ተመራማሪዎችም ወደ አካባቢው በመሄድ ባደረጉት ምርምር የአካባቢው ነዋሪዎች የሚናገሩትን አረጋግጠናል፤ የመሬቱ ከፍታ በየዓመቱ እየጨመረ ነው ይላሉ።

የኖቲንግሃም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2015 እስከ 2017 ሲካሄድ በነበረው ጥናት ሁለት ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሬት በየዓመቱ በ2 ሳንቲ ሜትር ከፍታው እየጨመረ መሆኑ ተረጋግጧል።

የመሬቱ ከፍታ በምን ምክንያት እየጨመረ ነው የሚለው ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ተመራማሪዎች ግን ይህ ክስተት ሆን ብሎ የመጣ እንዳልሆነ እና ምናልባት አካባቢው ላይ ከፍተኛ የሆነ የውሃ ክምችት ሊኖር እንደሚችል ነው እየተናገሩ ያሉት።

እናም ይላሉ ተመራማሪዎች የአካባቢው አስተዳደር የሚያፈስ ውሃ አሊያም በአካባቢው የሚያልፍ የቆሻሻ ትቦ እያፈሰሰ ከሆነ ሊመረምሩት ይገባል፤ ይህ ከሆነ እና ከፈነዳ የሚያስከትለው ጉዳት የከፋ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

እንዲህ አይነት ክስተት በተፈጥሯዊ ሂደት የሚከሰት አይደለም፤ ስለዚህም በጥልቀት ቢጤንበት መልካም ነውም ብለዋል።

ምንጭ፦ www.odditycentral.com